Homeዜናና ወቅታዊዜናበፈረንሳይ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረበው ሴት ስፖርተኞች ሒጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ...

በፈረንሳይ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረበው ሴት ስፖርተኞች ሒጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞ ገጠመው

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በፈረንሳይ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በቀረበው ሴት ስፖርተኞችን ሒጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ ላይ ተቃውሞውን ያሰማው ትናንት ረቡዕ ነው፡፡  

የመብት ተሟጋቹ ተቃውሞ የመጣው ማክሰኞ እለት ቀኝ አክራሪዎች በቁጥር የሚበዙበት የፈረንሳይ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት፤ የቀረበለትን ሙስሊም ሴት ስፖርተኞች ሒጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን የሕግ ረቂቅ ከደገፈ በኋላ ነው፡፡ በረቂቅ ሕጉ መሠረት ፈረንሳይን በአማተርም ሆነ በፕሮፌሽናል ውድድሮች ላይ የሚወክሉ ስፖርተኞች ሒጃብን ጨምሮ ሁሉንም የሃይማኖት ትዕምርት እንዳያደርጉ ክልከላ ይጣልባቸዋል፡፡

ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ሕግ፤ ሕግ ሆኖ ተግባራዊ እንዲደረግ ከታችኛው ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ተጨማሪ ድምጽ ማግኘት ቢኖርበትም የቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች ጠንካራ ግፊት እያደረጉ በመሆኑ ውድቅ ይደረጋል የሚል ግምት አለመኖሩን የሀገሪቱ መገናኛ ብዘኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ማክሰኞ ምሽት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በተሰጠ ድምጽ ረቂቅ ሕጉ 210 ድጋፍ ሲያገኝ፤ 81 ተወካዮች ተቃውመውታል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ክልከላውን “አድልዎ የተሞላና የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ነው” ብሎታል፡፡ ድርጅቱ በፈረንሳይ ሴት ስፖርተኞችን ሒጃብ ለመከልከል የሚደረገው ሙከራ የእስልምና ጥላቻን ያዘለ እና ሙስሊም ሴቶች የሚለብሱትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሙከራ መሆኑንም ገልጿል፡፡ መግለጫው፤ እንዲህ ዐይነቱ ሕግ ሙስሊም ሴቶችን በምትጨቁነው ፈረንሳይ የሚገኙ ሙስሊሞች “ቀድሞውኑ ሲጋፈጡት የቆዩትን የሃይማኖት እና የዘር መድሎ የሚያባብስ ነው” በሚል ሥጋቱን አጋርቷል፡፡  

ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል በተጨማሪ የሀገሪቱ ግራ ዘመም ፖለቲከኞችም ረቂቅ ሕጉን እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ረቂቁ ሕግ ሆኖ የሚጸድቅ ከሆነ እ.አ.አ በ1905 የሕሊና ነጻነትን ለመጠበቅ የወጣውን ሕግ የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሶሻሊስት ፓርቲ ተወካዩ ፓትሪክ ካነር፤ ረቂቁን የደገፉ አካላትን “መሠረታዊ መርሆችን በመጠቀም ፀረ ሙስሊም ትርክት እንዲዳብር በማድረግ በሀገሪቱ ውስጥ ግራ መጋባትን እና የተሳሳተ አመለካከት እንዲስፋፋ እያደረጋችሁ ነው” ሲሉ ነቀፌታ ሰንዝረዋል፡፡ የአረንጓዴ ፓርቲ አባሉ ማቲልድ ኦሊቪየር በበኩላቸው “ሙስሊም ሴቶችን በቀጥታ ዒላማ በማድረግ ከስፖርት እንዲገለሉ እያደረጋችሁ ነው” ብለዋል፡፡

በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ሒጃብ እንዳይለበስ ክልከላ ለመጣል ሕግ ያዘጋጀችው ፈረንሳይ፤ ባለፈው ዓመት ባዘጋጀችው የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ወቅት አትሌት ሱንካምፓ ሲይላ፤ በመክፈቻ ሥነ ሥርአት ላይ ሒጃብ ለብሳ እንዳትገባ ክልከላ ጥላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የተላለፈው የሀገሪቱ ውሳኔ በተመሳሳይ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ትችት የተነዘረበት ቢሆንም፤ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እናራምደዋለን የሚሉትን የሴኩላሪዝም ፖሊሲ ተገን በማድረግ በአቋም ጸንተዋል፡፡

አምነስቲ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴም የፈረንሳይን ውሳኔ በዝምታ በማለፉ ትችት ሰንዝሮበት ነበር፡፡ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ አትሌቶቼ ሒጃብ አድርገው መወዳደር አይችሉም ያለችው ፈረንሳይ፤ በውድድሩ ላይ የሒጃብ ክልከላ የጣለች ብቸኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ሆናለች፡፡

ፈረንሳይ ከአጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 9 በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ ይሁን እንጂ በ2019 በወጣ ሪፖርት ከጠቅላላ ሙስሊም ማኅበረሰቡ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት ‘በሃይማኖታችን ምክንያት መገለል ይደርስብናል’ የሚል እምነት አላቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular