Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበረመዳን ዋዜማ - ሐሙስ የካቲት 13/2017

በረመዳን ዋዜማ – ሐሙስ የካቲት 13/2017

የተከበረው የረመዳን ወር ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ይጀምራል፡፡ በእነዚህ ቀናት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ሀገራት “በረመዳን ዋዜማ ምን አዲስ ኸበር ተሰማ?” ብለን እናጣራለን፡፡ የሰማነውን መልሰን ለእናንተ እናደርሳለን፡፡ ለዛሬ የሰማናቸው ተከታዮቹ ናቸው፦

1/ ሱዳን፦ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በረመዳን ወር የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ አቅርቧል። የኅብረቱ ጥሪ የመጣው ከሰሞኑ በሀገሪቱ መደበኛ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሚደረገው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ ነው። በሱዳን ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በረመዳን ወቅት ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሙሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጎን በመሰለፍ በዐብዱልፈታህ አል ቡርሐን ውንጀላ የሚቀርብበት የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መንግሥት፤ ተፋላሚ ኃይሎቹ ለሰብዓዊ አቅርቦት ሲባል ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል።

2/ ኢንዶኔዥያ፦ የኢንዶኔዥያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት የረመዳንን መምጣት ተከትሎ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ትዕዛዙ የመጣው ባለፉት ቀናት የኢንዶኔዥያ ስታትስቲክስ ቢሮ ካወጣው ሪፖርት በኋላ ነው። መሥሪያ ቤቱ መንግሥት በተለይ ቁጥጥር ሊያደርግባቸው ይገባል ካላቸው መካከል ዘይት እና ስኳር ይገኙበታል ያለው አንታራ ኒውስ ነው።

3/ ደቡብ ሱዳን፦ የደቡብ ሱዳኑ ብሉናይል ግዛት አስተዳዳሪ አሕመድ አል ኦምዳ ባዲ፣ በረመዳን ወር ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ መታወጁን አስታውቀዋል። የሱዳን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ማክሰኞ ዕለት የታወጀው ሰዓት እላፊ የተጣለው ተባብሶ በቀጠለው የሱዳን ጦርነት በአጎራባች አካባቢዎች ንጹሓን በመገደላቸው ነው። የሰዓት እላፊው የሚተገበረው ከምሽት 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት ድረስ ነው።

4/ ኳታር ቻሪቲ የተሰኘው የረድዔት ድርጅት ለ1446 ዓ.ሂ በመላው ዓለም 40 ሀገራት የሚገኙ 4.5 ሚሊዮን ምንዱባንን ለመርዳት ያለመ የረመዳን ዘመቻ ይፋ ማድረጉን አሳውቋል። የረድዔት ድርጅቱ ዘመቻው በተለይ እገዛ የሚፈልጉ ከሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን በኃላፊዎቹ በኩል ገልጿል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular