በረመዳን ዋዜማ – 1

የተከበረው የረመዳን ወር ከዐስር ቀናት በኋላ ይጀምራል፡፡ በእነዚህ ቀናት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ሀገራት “በረመዳን ዋዜማ ምን አዲስ ኸበር ተሰማ?” ብለን እናጣራለን፡፡ የሰማነውን መልሰን ለእናንተ እናደርሳለን፡፡ ረመዳንን በጋራ እንቀበል፡-

1/ ሳዑዲ ዐረቢያ፡- በዘንድሮ ረመዳን በሁለቱ ቅዱሳን ሥፍራዎች በሚገኙ መስጂዶች የተራዊሕ ሰላት በዐሥር ረከዐ እንዲወሰን ውሳኔ ተላልፏል። በመካ መስጂድ አልሐረም እና በመዲና የመልዕክተኛው መስጂድ የተራዊሕ ሰላት የሚመሩ ኢማሞችም ሥም ይፋ ተደርገዋል። በመስጂድ አልሐረም ለተራዊሕ እና ተሐጁድ የተመረጡት ሰባት ኢማሞች ሸይኽ ዓብዱረሕማን አስሱደይስ፣ ሸይኽ ማሒር አልሙዓይቅሊ፣ ሸይኽ በንዳር በሊላህ፣ ሸይኽ ያሲር ደውሰሪ፣ ሸይኽ በድር አል ቱርኪ፣ ሸይኽ ወሊድ አል ሸምሳን ናቸው። ዕውቁ ኢማም ሸይኽ ሳዑድ አል ሹረይም ለተከታታይ ሦስተኛ ዓመት በሐረም የተራዊሕ ሰላት ከሚመሩ ኢማሞች መካከል ሥማቸው ሳይካተቱ መቅረቱን የኢንሳይድ ሐረመይን መረጃ ያመለክታል።

2/ ሳዑዲ ዐረቢያ፡- ሸይኽ ዓብዱረሕማን አስሱደይስ በረመዳን ወር 27ኛውን ሌሊት የተሐጁድ ዱዓ እንዲያደርጉ ተመርጠዋል፡፡ በዚሁ እለት የሚኖረውን የተራዊሕ ሰላት በኢማምነት የሚመሩት ሸይኽ ያሲር ደውሰሪ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ የቀጥታ ሥርጭቱ በመላው ዓለም በቴሌቪዥንእንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚተላለፍ ሳዑዲ ዐረቢያ አስታውቃለች፡፡

3/ የመን፡- በየመን የሚገኘው አምራን ግዛት የረመዳን ወር መምጣቱን ተከትሎ 180 እስረኞች በምሕረት እንዲፈቱ ውሳኔ አሳልፏል። የተፈቱት እስረኞች የእስር ጊዜያቸውን 3/4ኛ የጨረሱ መሆናቸውን አሳውቋል።

4/ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፡- ሻርጃህ 35ኛውን ዙር የሻርጃህ የረመዳን ፌስቲቫል በመጪው ቅዳሜ ታስተናግዳለች። ለዘጠኝ ቀናት የሚቆየው የረመዳን ፌስቲቫል በሻርጃህ ንግድ ምክር ቤት የተዘጋጀ መሆኑን የዘገበው ዛውያ ድረ ገጽ ነው።

5/ ኬንያ፡- ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው የኬንያው ፕሪሚየር ባንክ፣ በረመዳን ወር ለ5 ሺሕ ቤተሰቦች የኢፍጣር ድጋፍ ለማድረግ ከዘካ ኬንያ ጋር ባንድነት እየሠራ መሆኑን አሳውቋል። ለሁለተኛ ጊዜ ለምዕመናን የሚደርሰው የባንኩ ድጋፍ በመጪው እሑድ የሚከፋፈል መሆኑን የሀገሪቱ ጋዜጣ ስታንዳርድ ዘግቧል። የባንኩ ኃላፊ የሆኑት የህያ ዳሒር “በረከት በሞላው የረመዳን ወር እያንዳንዱ ቤተሰብ ራሱን ችሎ ማፍጠር መቻሉን የማረጋገጥ ግዴታ አለብን” ብለዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular