Homeዜናና ወቅታዊዜናግብጽ ፍልስጤማዊያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ ለመገንባት “አጠቃላይ ዕቅድ” ማዘጋጀቷን ፕሬዝዳንቷ ተናገሩ

ግብጽ ፍልስጤማዊያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ ለመገንባት “አጠቃላይ ዕቅድ” ማዘጋጀቷን ፕሬዝዳንቷ ተናገሩ

የግብጽ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ፤ ሀገራቸው ፍልስጤማውያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ ለመገንባት “አጠቃላይ ዕቅድ” ማዘጋጀቷን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት ከዓለም የአይሑድ ኮንግረስ መሪ ሮናልድ ላውደር ጋር በካይሮ በተገናኙበት ወቅት ነው።

በአልሲሲ እና በላውደር መካከል የተደረገው ውይይት፤ ቀጣናውን ወደመረጋጋት ለመመለስ በሚያስችሉ መንገዶች እና ግብፅ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት ላይ በምታደርጋቸው ጥረቶች ላይ ያተኮረ እንደነበር የአናዶሉ ኤጀንሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ፤ በውይይቱ ላይ የምርኮኞች እና እስረኞች ልውውጥ እንዲሁም የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ የሚገባበት ሁኔታ ተነስቷል፡፡ የግብፅ ፕሬዝዳንት “የጋዛን መልሶ ግንባታ መጀመር እና ነዋሪዎቿ ከመሬታቸው እንዳይፈናቀሉ ማረጋገጥ” አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሐማስ እና እስራኤል የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስቀጠል ኃላፊነት የተሞላበት ርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነት ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ አያይዘውም የግጭቱ መስፋፋት ሁሉንም ወገኖች እንደሚጎዳ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ ዐብዱልፈታህ አልሲሲ እ.አ.አ በሰኔ 4፣ 1967 በተሰመረውን ድንበር መሠረተ ያደረገ ምሥራቅ ቁድስን ዋና ከተማዋ ያደረገ የፍልስጤም ሀገረ መንግሥት መመሥረት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብቸኛው ዋስትና ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላ ላውደር በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማስፈን ግብፅ የምትጫወተውን የመሪነት ሚና በመገንዘብ በተለያዩ አግባብነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከሀገሪቱ ጋር ለመመካከር ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ያወጡት መግለጫ ያመለክታል፡፡

የግብጽ ፕሬዝዳንት ንግግር የመጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ጋዛን ለመቆጣጠር ሕዝቡን በሌሎች ሀገራት የማስፈር ሐሳብ እንዳላቸው ከተናገሩ በኋላ ነው። በዚህ ዕቅድ ላይ ፍልስጤማዊያንን ለማስፈር ከታጩት ሀገራት መካከል ግብጽ ተጠቅሳለች፡፡ ከዕቅዱ ይፋ መደረግ በኋላ ሐሳቡን በተደጋጋሚ ውድቅ ያደረገችው ግብጽ፤ ፕሬዝዳንቷ ዓብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ዋይት ሐውስ ጉዞ ያደርጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እንዲዘገይ መደረጉን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ የአል ሲሲ ጉዞ እንዲዘገይ የተደረገበት ምክንያት ላይ ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡

በትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎችን ለማስፈር የታጨችው ግብፅ፤ በየዓመቱ ከአሜሪካ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ የምታገኝ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ እ.አ.አ ከ1946 አንስቶ በአጠቃላይ 97 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ከአሜሪካ ያገኘችው ሲሆን፣ የሚደረግላት የገንዘብ ድጋፍ በከፍተኛ መጠን የጨመረው በ1979 ከእስራኤል ጋር ከፈረመችው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማስፈን በሚል የተፈረመው ስምምነት፤ ዋንኛ አደራዳሪ የአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ነበሩ፡፡

ሰሞነኛው የትራምፕ እቅድ በሙስሊሙ እና ዐረቡ ዓለም እንደሁም ሌሎች በርካታ አገሮች የዘር ማጥፋት ነው በሚል ውድቅ ተደርጓል፡፡ አወዛጋቢው የትራምፕ ሀሳብ ይፋ የተደረገው ከሦስት ሳምንት በፊት በጋዛ ተግባራዊ የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular