Homeዜናና ወቅታዊዜናሳዑዲ ዐረቢያ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በስታዲየም አልኮል ለሽያጭ እንደማይቀርብ በይፋ አስታወቀች

ሳዑዲ ዐረቢያ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በስታዲየም አልኮል ለሽያጭ እንደማይቀርብ በይፋ አስታወቀች

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን እ.አ.አ በ2034 የምታስተናግደው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ በስታዲየሞች አልኮል ለሽያጭ እንደማይቀርብ በይፋ ያሳወቀችው በዩናይድ ኪንግደም አምባሳደሯ በኩል ነው፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የሳዑዲ ዐረቢያ አምባሳደር ኻሊድ ቢን ባንደር ቢን ሡልጣን አሳዑድ፤ ይህንኑ ኤልቢሲ ለተሰኘው የብሪቲሽ ኦንላይን ራድዮ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ በቆይታቸው ለመዝናናት የግድ አልኮል አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያ የሁሉንም ሀገራት ባሕል እና ማንነት ታከብራለች ሲሉ የተናገሩት ኻሊድ፤ እኛም ለሌሎች ፍላጎት በመገዛት ባሕል እና ማንነታችንን የመለወጥ ፍላጎት የለንም ብለዋል፡፡

አልኮል በስታዲየሞች ለሽያጭ እንደማይቀርብ በይፋ ያሳወቀቸው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ ከዚህ ቀደም በይፋ ባይሆንም ፍቃድ እንደማትሰጥ ከፊፋ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሳለች በሚል ሲነገር ቆይቷል፡፡ የአሁኑ የአምባሳደሩ ንግግር በይፋ በሀገሪቱ ባለሥልጣን ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑን የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡

ፊፋ ውድድሩ ከአስር ዓመት በኋላ በሀገሪቱ እንደሚስተናገድ የገለጸው በታኅሣሥ ወር ነበር፡፡ ከፊፋ ጋር ቅርበት አላቸው የሚባሉት የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት፤ በሀገሪቱ ብሔራዊ የነዳጅ አምራች “አርማኮ” በኩል ከአወዳዳሪው አካል ጋር ለአራት ዓመት የሚቆይ የ320 ሚሊዮን ፓዉንድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ የፊፋን የክለቦች ውድድር የቀጥታ ሥርጭት ለመውሰድ “ዳዝን” በተሰኘው ኩባንያ በኩል 800 ሚሊዮን ፓዉንድ ክፍያ ፈጽሟል፡፡

የዓለም ዋንጫ ውድድር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው በ15 ስታዲየሞች ነው፡፡ እነዚህ ስታዲየሞች የሚገነቡት በጂዳ፣ አልኹበር፣ አብሃ፣ ሪያድ እና በልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን የቪዥን 2030 ዕቅድ ውስጥ ግንባታዋ ይከናወናል በተባለችው ኑዩም ከተሞች ነው፡፡

የዓለም ዋንጫ ከሁለት ዓመት በፊት በተመሣሣይ በሌላኛዋ እስላማዊ ሀገር ኳታር መስተናገዱ የሚታወስ ነው፡፡ ኳታር በውድድሩ ወቅት በስታዲየሞች የአልኮል መጠጥ ክልከላ ጥላ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular