የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥልጤ ዞን በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የተገነቡ “የተወሰኑ” መኖሪያ ቤቶችን በቀጣይ ሣምንት ለነዋሪዎች ሊያስረክብ መሆኑን በዛሬው እለት የገለጸው በፕሬዝዳንቱ በኩል ነው፡፡
መኖሪያ ቤት የተገነባላቸው ዜጎች ከሁለት ሣምንታት በኋላ የሚጀምረውን የረመዳን ጾም “በቤታቸው ገብተው ስብራታቸው ተጠግኖ የዒባዳ ወሩን እንዲያሳልፉ” መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሡልጣን አማን ይህን የገለጹት፤ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 6/2017 በአዲስ አበባ ከተማ ስቴይ ኢዚ ሆቴል “የረመዳንን መምጣት አስመልክቶ ከዓሊሞች፣ ኢማሞች እና ዱዓቶች ጋር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ” ላይ ነው፡፡ በንግግራቸው መኖሪያ ቤቶቹ የተገነቡት “ከዞኑ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመተባባር” መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የከተማው ከፍተኛ ምክር ቤት በሥልጤ ዞን ባለፈው ዓመት ክረምት ወር በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን “ወደ ቀድሞ የአኗኗር ዘይቤ ለመመለስ” ይረዳል ያለውን መኖሪያ ቤት ለማስገንባት 3 ሚሊዮን 990 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉን ያሳወቀው ጥቅምት 27/2017 ነበር፡፡ በዚህ ወቅት እንደተገለጸው በገንዘብ ድጋፉ ይገነባሉ ተብለው በእቅድ የተያዘው 14 መኖሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ በዛሬው እለት ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ በቀጣይ ሣምንት ለነዋሪዎች የሚያስረክቧቸውን ቤቶች ብዛት “የተወሰኑ” ብለው ከመግለጽ ውጪ ትክክለኛውን ቁጥር አልጠቀሱም፡፡
በሥልጤ ዞን ጎፍለላ ቀበሌ ቀድሞ የተከሰተው ጎርፍ፤ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመዛመቱ ከአንድ ሺሕ በላይ አባወራዎችን ያፈናቀለ እንደነበር የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ በወቅቱ ባወጣው መረጃ ገልጿል፡፡ የጎርፍ አደጋው ቀድሞ ከተከሰተበት ጎፍለላ በተጨማሪ በአሹቴ፣ ባሎ ቀሪሶ፣ ምዕራብዬ እየቆጬ፣ ምሥራቅ እየቆጬ እና ሰዳ ጎራ ቀበሌዎችን ያዳረሰ ነበር፡፡ በጎርፍ አደጋው ከወደሙ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በርካታ የቤት እንስሳት ሞተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












