ሥመጥሩው የግብጽ ዩኒቨርሲቲ አል-አዝሃር፤ ሙስሊም ሀገራት ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ለማፈናቀል የሚደረገውን “ማንኛውንም ሙከራ እንዲቃወሙ” ጥሪ ያቀረበው አዲስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው መላው ዓለም “የፍልስጤማዊያን መብት እንዲከበር ከጎናቸው እንዲቆም” እንዲሁም “ቁድስን ዋና ከተማ ያደረገ የራሳቸው ሀገር እንዲመሠርቱ ሊደግፋቸው ይገባል” ብሏል፡፡
የአል-አዝሃር ዩኒቨርሰቲ ጥሪ የመጣው፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎችን በጎረቤት ሀገራት በማስፈር ሥፍራውን የመውረስ እቅድ እየተደጋገመ ባለበት ወቅት ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሲናገሩት የቆዩትን ሐሳብ፤ በዋይት ሐውስ ጋብዘው ለሠፈራው ከታጩት ሀገራት መካከል ለጆርዳኑ ንጉሥ ዐብደላህ ደግመውታል፡፡
ዕቅዱን የተቃወመው ዩኒቨርሲቲው፤ “ማንም ቢሆን የፍልስጤም ሕዝብ የማይጨበጡ ምክረ ሐሳቦችን እንዲቀበል ግፊት የማድረግ ወይም የማስገደድ መብት የለውም” ብሏል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ የሃይማኖት መምሕራን ፍልስጤማዊያንን ለመከላከል ድምጽ እንዲያሰሙ ጠይቋል፡፡ ከመምሕራኑ በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት ተቆርቋሪነት እንዲያሳዩ ተጠይቀዋል፡፡
መግለጫው አያይዞም “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተጨቆኑ እና ለግፉአን ድጋፍ አለመስጠቱ” በሁሉም አቅጣጫ ወደ አለመረጋጋት የሚገፋና “ምድርን የጉልበታም መፈንጫ” የሚያደርግ ሰው ሲል ጉዳዩ ችላ መባል ያለበት ጉዳይ አለመሆኑን አስጠቅቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው መግለጫ ግብጽም በተመሳሳይ ተቃውሞዋን እንድታሰማ ጠይቋል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ የቀረበው የጋዛን መሬት የመውረስ ዕቅድ፤ በይፋ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ሙስሊም እና ዐረብ ሀገራት ተቃውሞ እየቀረበበት የሚገኝ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህን ዕቅድ የገለጹት ቢያንስ 48 ሺህ 200 ፍልስጤማዊያንን የቀጠፈውን የእስራኤል ጥቃት ያስቆመ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
የሙስሊሙ ዓለም ከፍልስጤማዊያን ጎን እንዲቆም ጥሪ ያቀረበው አል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ፤ መቀመጫውን ካይሮ በማድረግ በሙስሊሙ ዓለም የሃይማኖት ትምሕርት ማዕከል በመሆን የሚታወቅ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












