የጆርዳኑ ንጉሥ ዓብደላ ዋይት ሐውስ ደርሶ ከትራምፕ ለመነጋገር የመጀመርያው የዐረብ ሀገር መሪ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትራምፕ ለሁለተኛው ጊዜ በጨበጡት ሥልጣን ማግሥት ያስነሱትን ‘የጋዛን እንወርሳለን’ ሐሳብ ተከትሎ የተደረገው የሀገሪቱ ንጉሥ ጉብኝት፤ ሰውዬውን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ክስተት ያለው ሆኖ አልፏል፡፡ የንጉሡ የአሜሪካ ጉብኝት የመጣው፤ ትራምፕ ጋዛን ከነዋሪዎቿ የማጽዳት እቅድ ሲያቀርቡ፤ አሠፍራለሁ ካሉባቸው ሀገራት መካከል አንደኛዋ የእርሳቸው ሀገር መሆኗን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነበር፡፡
ዕቅዱ በተሰማበት ጊዜ ሐሳቡን ውድቅ ያደረገችው ጆርዳን፤ በዋይት ሐውስ በትራምፕ ፊት ንጉሡን አቅርባ ጉዳዩን እንዴት ልታስተናግደው ትችላለች የሚለው ጉዳይ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ጊዜው ደርሶ ከአሜሪካ በየዓመቱ የበጀቷ ዐሥር በመቶ የሚሸፈንላት ሀገር ንጉሥ ዋይት ሐውስ ከትራምፕ አጠገብ ሲቀመጡ፤ ሀገራቸው ቀድሞ ስታንጸባርቅ የነበረውን አስተያየት መድገም ተስኗቸው በግራ መጋባት ውስጥ ትራምፕ የሚናገሩትን ሁሉ ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ከመስማት ውጪ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ አሳይተዋል፡፡ ትራምፕ ግን ከ15 ቀናት በላይ ሲደጋግሙት የቆዩትን ጋዛን የማጽዳትና የመውረስ ምኞት አሁንም እንደ ዘበት ደግመውታል፡፡
በሥፍራው የተገኙት ጋዜጠኞች ባለፉት ሳምንታት ሲጠየቁ እንደነበረው ሁሉ ለፕሬዝዳንቱ ‘የፍልስጤምን ሕዝብ የት ቦታ ለማሥፈር ነው የሚፈልጉት?’ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በሰጡት ምላሽ “ከግብጽ እና ጆርዳን ቁራሽ ወስደን፤ ሌላም ቦታ ቢሆን እዚያና እዚህ አድርገናቸው ይኖራሉ” ብለዋል። ትራምፕ “ውስብስብ” አለመሆኑን የጠቀሱትን የጋዛን መጠቅለል ጉዳይ፤ ሲያሳኩት የመካከለኛው ምሥራቅ “በዘመኑ ተመልክቶት የማያውቀውን ሰላም የሚያስገኝለት ነው” የሚል ሐሳብ አክለውበታል፡፡ ሥፍራውን [ጋዛን ማለታቸው ነው] አሜሪካ ከፍልስጤማዊያን ስትወርሰው ለሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ይሆናል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በዚህ ቆይታ ወቅት ከጋዜጠኞች በኩል የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ ጆርዳን የጋዛ ነዋሪዎችን ለመቀበል ፍቃደኛ ባትሆን አሜሪካ ለሀገሪቱ ‘የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ታቋርጥ እንደሆነ’ የሚጠይቀው ነው፡፡ ሀገራቸው ከጆርዳን በተጨማሪ ሌላኛዋ ፍልስጤማዊያንን ታሠፍራለች በሚል የተጠቀሰችው ግብጽ ጭምር ከአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በማስታወስ፤ “በዚህ ማስፈራራት አልፈልግም፤ የእኛ ግንኙነት ከዚህ በላይ እንደሆነ አምናለሁ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ስለ ጉዳዩ ቆፍጠን ብለው [በፍልስጤም – ካናዳዊቷ የሚድል ኢስት ዐይ ዘጋቢ ያስሚን አሰብዐዊ አገላለጽ] በተለመደው ‘Trumpian fashion’ ድፍረት የሞላው ማብራሪያ ሲሰጡ፤ አጠገባቸው የተቀመጡት ንጉሥ ስላቀረቡት ሐሳብ ቀድሞ እንዳደረጉት በተቃርኖ መቆም ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡ ሐሳባቸውን መግለጽ የቻሉትም ከጋዜጠኞች በነበረው የመጨረሻ ደቂቃ ቆይታ ወቅት ነው፡፡
በተናገሩበት ቅጽበትም ቢሆን በተመጠኑ ቃላት ከትራምፕ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቅቀው መግለጫውን ቋጭተዋል፡፡ በትራምፕ ተደጋግሞ ለተነሳው ፍልስጤማዊያንን በጆርዳን የማሥፈር እቅድ ላይ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው በተጠየቁበት ወቅትም የተድበሰበሰ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ቀድሞ ሲንጸባረቅ የነበረውን ጉዳዩን የተቃወመ አስተያየት በድጋሚ የተቃረነ ሆኗል፡፡
ነገር ግን ንጉሡ ከትራምፕ አጠገብ ተቀምጠው ማንጸባረቅ የከበዳቸውን አስተያየት መግለጫው ከተጠናቀቀ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሥፍረውታል፡፡ በዚህም ጆርዳን የጋዛ ነዋሪዎችን በማፈቀናቀል ጉዳይ “በፍጹም አይደረግም” በሚል “የማይናወጥ” አቋም እንዳላት ገልጸዋል፡፡ አክለውም ዐረብ ሀገራት ጋዛን በተመለከተ የራሳቸውን አማራጭ ምክረ ሐሳብ ይዘው እንደሚመጡ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የዐረብ ሀገራት የጋዛ እቅድ በሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይመን ሳፋዲም በተመሳሳይ ተንጸባርቋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ አንዳችም ማብራሪያ የተሰጠበት አይደለም፡፡
አልጀዚራ የአሜሪካ እና ጆርዳን መሪዎችን የዋይት ሐውስ ውይይት በተመለከተ ባወጣው ዘገባ፤ የትራምፕ የጋዛን እንጠቀልላለን እቅድ ሌላ አጀንዳ ለማሳካት የቀረበ እንደ መደራደሪያ ሥልት የተያዘ መሆኑን በመጠቆም፤ ዐረብ ሀገራት ይህን ለማክሸፍ ግን በጋዛ ምትክ ወሮታ ሊጠይቁ እንደሚገባ የሚከራከሩ ተንታኞች መኖራቸውን ጽፏል፡፡ ሀገራቱ በዚህ መንገድ መደራደር የማይችሉ ከሆነ በጋዛ ጉዳይ ትራምፕን በዲፕሎማሲ መርታት የሚታሰብ አለመሆኑንም አስነብቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












