በአፋር በሃላይዳጌ እጩ ብሔራዊ ፓርክ ከሦስት ቀናት በፊት የተቀሰቀሰውን የሰደድ እሳት መቆጣጠር እንደተቻለ፤ የክልሉ የቱሪዝም እና ፓርኮች ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ሐሰን ያዮ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናገሩ፡፡ እሳቱን “ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል” የሚለውን ለማረጋገጥ 24 ሰዓት መሙላት እንደሚኖርበትም ተገልጿል፡፡
በክልሉ በሃላይጌ እጩ ብሔራዊ ባንክ ሰደድ እሳት የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የካቲት 1/2017 እንደነበር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ እሳቱ ለሁለት ቀናት ቆይቶ ትናንት ሰኞ መቆጣጠር እንደተቻለ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዛሬ ማክሰኞ የካቲት 4/2017 እኩለ ሌሊት ገደማ 24 ሰዓት እንደሚሞላው አስረድተዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሪፖርት የሚዛመተውን እሳት መቆጣጠር ቢቻልም ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል ማለት የሚቻለው ግን ከተጠቀሰው ሰዓት በኋላ ነው ብለዋል፡፡
የሃላይዳጌ ብሔራዊ ፓርክ በዚህ ዓመት ብቻ ለአምስተኛ ጊዜ ተመሳሳይ የእሳት አደጋ ያስተናገደ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከደረሱ የእሳት ቃጠሎዎች ውስጥ ሁለቱ የተከሰቱት በከሰል አክሳዮች እና በተጣለ ሲጃራ ምክንያት እንደሆነ ሪፖርት መቅረቡ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ቅዳሜ ለተቀሰቀሰው እሳት መንስኤውን እስካሁን ማወቅ እንዳልተቻለ ለ“ሚንበር ቲቪ” የተናገሩት አቶ ሙሐመድ ሐሰን ያዮ፤ መንስኤውን ለማወቅ አጣሪ ቡድን ነገ ረቡዕ ለሥምሪት እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡ ቡድኑ የሚያደርገውን ዳሰሳ ተከትሎ መንስኤውን ጨምሮ የደረሰውን ውድመት ማወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡
ከ1 ሺሕ 99 ገደማ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሥፋት ያለው ሃላይዳጌ እጩ ብሔራዊ ፓርክ፤ ከ1965 ጀምሮ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ሥፍራው የ325 የዕጽዋት ዝርያ፣ የ244 የአእዋፍ ዝርያ እንዲሁም ከ42 በላይ አጥቢ እንስሳት መኖሪያ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












