Homeዜናና ወቅታዊዜናየጋዛ ነዋሪዎችን ከቀዬ ለማፈናቀል በዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን እቅድ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን “ረብ የለሽ”...

የጋዛ ነዋሪዎችን ከቀዬ ለማፈናቀል በዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን እቅድ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን “ረብ የለሽ” ሲሉ አጣጣሉት

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን የጋዛ ነዋሪዎችን ከቀዬ ለማፈናቀል በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን እቅድ፤ “ረብ የለሽ” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ኤርዶጋን ይህን የተናገሩት ወደ ማሌዥያ ካደረጉት በረራ አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡትን ሐሳብ “ለወሬ ፍጆታ እንኳን የማይበቃ” መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ፍልስጤማዊያንን ለበርካታ ሺሕ ዓመታት ከኖሩበት ጋዛ ከተማ “በግዳጅ ማፈናቀል የሚችል አንዳችም ኃይል የለም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ጋዛ ብቻ ሳይሆን ዌስት ባንክ እና ምሥራቃዊ የቁድስ ክፍል የፍልስጤማዊያን ሕጋዊ መሬት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን አስተያየት የመጣው፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋግመው የጋዛ ነዋሪዎችን በጎረቤት ሀገራት በማስፈር፤ አካባቢውን “ማጽዳት” እንፈልጋለን የሚል ሐሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ትራምፕ ባለፉት ቀናት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲደጋግሙት የቆዩትን ይህን ሐሳብ፤ አሜሪካዊያን በሥፋት የሚታደሙትን ሱፐር ቦውል የተሰኘ ውድድር ለመከታተል ወደ ኦርሊየንስ እያቀኑ በነበረበት ወቅት ትናንት እሑድም አንስተውታል፡፡ የጋዛ አካባቢ ለሪስእስቴት አመቺ መሆኑን በመጥቀስ፤ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትም በግንባታው ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ንግግር መሬቱን ተቆጣጥረን የፍልስጤሙ ሐማስ እንዳይመለስ ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ትራምፕ ይህን ሲናገሩ ከሐማሱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንደኛው ኸሊል አልሐያ፤ ከነበሩበት የኢራኗ ቴሕራን ከተማ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በኢራን አብዮት 46ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ የተገኙት አልሐያ፤ “ምዕራባዊያን ከዚህ ቀደም የወጠኑትን ስናከሽፈው እንደቆየነው፤ ይህን እቅድ በተራው እናፈራርሰዋል” ብለዋል፡፡

በትራምፕ እቅድ ቀድሞ ፍልስጤማዊያን ከጋዛ ተነስተው ይሠፍሩበታል የተባለው በጆርዳን እና ግብጽ የነበረ ቢሆንም፤ በሁለቱም ሀገራት ውድቅ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሳዑዲ ዐረቢያን በሥም በመጥቀስ፤ “ሀገሪቱ ከፈለገች ነጻ ፍልስጤምን በመሬቷ መመሥረት ትችላለች” የሚል ትንኮሳ ያዘለ ንግግር ሲያደርግ፤ ሳዑዲ ንግግሩን በማውገዝ መግለጫ አውጥታለች፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ፍልስጤማዊያን በመሬታቸው ባለ መብት መሆናቸውን በመግለጽ፤ በእስራኤል ጭካኔ አዘል ምኞት የሚፈናቀሉ ሕዝቦች እንዳልሆኑም ሰፍሯል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ወቅታዊ ድርጊት በጋዛ የፈጸመውን የጦር ወንጀል የመሸፋፈን ዓላማ ያለው ነው ብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት ግብጽ የፍልስጤምን ግዛት አስመልክቶ የዐረብ ሊግ ሀገራትን አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቷ ታውቋል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የተጠራው ጉባዔ ይፋ የተደረገው ትናንት እሑድ መሆኑን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳወጣው መረጃ ከሆነ፤ ስብሰባው በካይሮ የሚካሄድ ሲሆን፣ አስተባባሪዋ ደግሞ የወቅቱ የዐረብ ሊግ ሊቀመንበር ባህሬን ትሆናለች፡፡ መግለጫው ጉባዔውን ለማካሄድ የተወሰነው፤ ግብፅ ባለፉት ቀናት ከወንድማማች ዐረብ አገራት ጋር በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ምክክር ካደረገች በኋላ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እያራመዱት የሚገኙት ጋዛን የማጽዳት ሐሳብ፤ ከሙስሊም እና ዐረብ ሀገራት በተጨማሪ በአሜሪካዊያን ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ሲቢኤስ በዩጎቭ በኩል ባሠራው የሕዝብ አስተያየት መሠረት፤ 47 በመቶ አሜሪካዊያን ሐሳቡን “መጥፎ” ነው ሲሉ ፈርጀውታል፡፡

አሜሪካ የጦር ድጋፍ የምታደርግላት እስራኤል በጋዛ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ 45 ሺሕ ፍልስጤማዊያንን መግደሏ የሚታወቅ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

.

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular