የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በግል የአውሮፕላን ትኬት ቆርጠው በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ምዕመናን ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ እንደ ምክር ቤቱ ከሆነ፤ ምዝገባው የተጀመረው ዛሬ ጁመዓ ጥር 30/2017 ነው፡፡
የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊው ሐጅ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድ፤ በተጀመረው ምዝገባ መጠቀም የሚፈልጉ ምዕመናን በተዘጋጁ ጣቢያዎች እንዲስተናገዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በግል ትኬት ቆርጠው በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለሚሳተፉ ምዕመናን የደርሶ መልስ የበረራ ሰዓት፣ መዳረሻ እና መመለሻ ከተማ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በሚያስቀምጠው መመርያ ብቻ የሚስተናገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት ከኢትዮጵያ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ምዕመናን ቁጥር 10 ሺሕ እንደሚሆን ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ገልጿል፡፡ ጥር 15/2017 በተጀመረው የሐጅ ምዝገባ፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ ጣቢያዎች የተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ1 ሺሕ 200 ደርሷል፡፡ ከምዕመናኑ መካከል ከ320 በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የምዝገባ ጣቢያ የተመዘገቡ መሆናቸውን የከተማዋ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዚህ ሳምንት አጋማሽ ይፋ አድርጓል፡፡
ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ምዝገባ ለማከናወን የሚያስፈልገው ከዘጠኝ ወር በላይ ግዜ ያለው ፓስፖርት፣ የቀበሌ እና ፋይዳን ጨምሮ ሌሎች ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲሁም መንጃ ፍቃድ ነው፡፡ ለሐጅ ምዝገባው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጁ የምዝገባ ጠቢያዎች ብዛት 30 መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቀደም ብሎ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
የሐጅ ምዝገባው ቀን መጨረሻ ሸዋል 30/1446 ዓ.ሂ (የካቲት 22/2017) እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












