Homeዜናና ወቅታዊዜናአሜሪካ፤ በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ከግብጽ ጎን ለመቆም የጋዛ ነዋሪዎችን የማስፈር ወሮታ ጠየቀች

አሜሪካ፤ በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ከግብጽ ጎን ለመቆም የጋዛ ነዋሪዎችን የማስፈር ወሮታ ጠየቀች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ በገባችበት ውዝግብ ከሀገሪቱ ጎን ለመቆም የጋዛ ነዋሪዎችን እንድታሠፍር ወሮታ እንደተጠየቀች የዘገበው አል ዐረቢ አል ጀዲድ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህን ሐሳብ ያቀረቡት፣ ከአራት ቀናት በፊት ወደ ካይሮ በማምራት ከግብጽ ባለሥልጣናት ጋር በመከሩበት ወቅት ነው። ዘገባው ሥማቸውን ያልጠቀሳቸው ወደ ካይሮ ያመሩ የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር ዐብዱልዓጢ እና የደኅንነት ኃላፊው ሐሰን ረሻድ ጋር ውይይት አድርገዋል። በዚህ ውይይት ላይ የጋዛ እንዲሁም የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ተነስቷል።

አል ዐረቢ አል ጀዲድ ለዘገባው ዋቢ ያደረጋቸው ምንጭ፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ጋር በገባችበት ውዝግብ ሀገራቸው ከጎን የምትቆመው በቅድመ ሁኔታ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ቅድመ ሁኔታው ባለፈው ሰሞን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡት የጋዛ ነዋሪዎችን በግብጽ የማስፈር መሆኑን ገልፀውላቸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ የሚገኘውን ሁሉንም ነገር የማጽዳት ዕቅድ እንዳላቸው የተናገሩት ከአስር ቀናት በፊት ነበር። ፕሬዝዳንቱ ይህን ንግግር በእነዚህ ቀናት ውስጥ ለሦስት ጊዜ በመደጋገም ለመጨረሻ ጊዜ ያነሱት የየእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በዋይት ሐውስ ተቀብለው ባናገሩበት ወቅት ነው። በዚህ መግለጫ ላይ ፍልስጤማዊያን ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ እንደሚፈልጉ በግልፅ ተናግረዋል።

ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ፣ ፍልስጤማዊያንን ማስፈር የሚፈልጉት በግብጽ እና ጆርዳን ገልጸው የነበረ ቢሆንም የሀገራቱ ባለሥልጣናት ዕቅዱን በይፋ ውድቅ አድርገውታል።

ይሁን እንጂ በዘገባው የተጠቀሱ በአሜሪካ መንግሥት እና ግብጽ ባለሥልጣናት መካከል የተደረገውን ውይይት የተከታተሉ ዲፕሎማት፣ ግብጽ አሁን የቀረበውን የትራምፕ ዕቅድ የዐረብ ሀገራት ትብብር ካላደረጉላት ለብቻዋ መጋፈጥ ይቸግራታል ብለዋል። እንደ ዲፕሎማቱ ከሆነ ትራምፕ የግብጽ ባለሥልጣናት በእምቢታ ቢፀኑም ጉዳዩን ለመግፋት ቀርጠኛ አቋም ይዘዋል። የግብጽ ባለሥልጣናት በውይይቱ ወቅት አሜሪካ የምትደግፋትን የእስራኤልን ደኅንነት ለማረጋገጥ አማራጭ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የግብጽ መንግሥት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ተደርጓል የተባለውን የሕዳሴ ግድብ እና የጋዛ ጉዳይ በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም። ሆኖም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ሙሐመድ አሺዋኒ፣ ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ለጋዜጠኞች በመግለፅ፣ ውይይቱን አዎንታዊ ነበር ብለውታል።

ከአሜሪካ ወሮታ የተጠየቀችው ግብጽ፣ ኢትዮጵያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከጫፍ በደረሰችበት የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ተደጋጋሚ ተቃውሞ ስታቀርብ የቆየች ነች። በኢትዮጵያ በኩል በግብጽ የሚቀርበው ተቃውሞ መሠረተ ቢስ እና የተለመደ የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ ነው በሚል ውድቅ የሚደረግ ነው፡፡ የግብጽ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ የግድቡን ቴክኒካዊ ጉዳዮች ወደ ፖለቲካ ይጠመዝዙታል በሚል በሌሎችም አካላት ትችት ይቀርብባቸዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular