Homeዜናና ወቅታዊዜናበሸገር ከተማ በፈረሱ መስጂዶች ዙርያ ከኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጋር ውይይት ማድረጉን...

በሸገር ከተማ በፈረሱ መስጂዶች ዙርያ ከኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጋር ውይይት ማድረጉን ጠቅላይ ም/ቤቱ አሳወቀ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በፈረሱ መስጂዶች ዙርያ ከኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ ዐብዲሳ ጋር ውይይት ማድረጉን ያሳወቀው በዛሬው እለት ነው፡፡ በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ተደርጓል በተባለው ውይይት፤ “ከሸገር ሲቲ ምሥረታ” ጋር በተገናኘ “የፈረሱት መስጂዶች በቶሎ አገልግሎት አለመጀመር” ጉዳይ መነሳቱ ተገልጿል፡፡  

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ከኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከአቶ ሽመልስ ጋር ውይይት አድርገዋል የተባለው ዛሬ ረቡዕ ጥር 28/2017 ነው፡፡ በዚህ ውይይት ርእሰ መስተዳድሩ ከከተማው ምሥረታ ጋር በተያያዘ “ፈርሰው በነበሩ መስጅዶች ዙሪያ በመንግሥት የተገባው ቃል ያለመረሳቱን” አንስተው መናገራቸው ተገልጿል፡፡

የመስጂዶቹ አገልግሎት በቶሎ አለመጀመሩ “ሒደቱ ጊዜ በመውሰዱ ነው” ሲሉ መናገራቸውን የገለጸው  ጠቅላይ ምክር ቤቱ፤ “ቃል በገባነው መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔውን ተግባራዊ እናደርጋለን” ማለታቸውንም አሥፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ “አጭር ጊዜ” በሚል ከመጥቀሳቸው ውጪ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ስለመኖሩ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡

በሌላ በኩል ርእሰ መስተዳደሩ “በክልሉ በሚኖሩ ሙስሊሞች ዙሪያ” ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች “ጠቃሚ የሆነ የጋራ ወይይት አድርገዋል” ተብሏል፡፡

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ግንቦት 15/2015 እንዳሳወቀው፤ በሸገር ከተማ አዲስ ማስተር ፕላን መነሻ ከ19 በላይ መስጂዶች መፍረሳቸውን ገልጾ ነበር፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ይህንኑ ቅሬታ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማቅረቡን ተከትሎ አመራሮቹ ከርእሰ መስተዳድር ሽመልስ ዐብዲሳ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፤ በከተማው መስጂዶች እንደሚገነቡ ቃል መግባታቸው ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular