Homeዜናና ወቅታዊዜናየትራምፕን የጋዛ ነዋሪዎች የማጽዳት ዕቅድ የሚቃወም ሠልፍ በዋይት ሐውስ ደጃፍ ተደረገ

የትራምፕን የጋዛ ነዋሪዎች የማጽዳት ዕቅድ የሚቃወም ሠልፍ በዋይት ሐውስ ደጃፍ ተደረገ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎችን በጎረቤት ሀገራት በማሥፈር ከተማዋን ለማጽዳት ያቀረቡትን ሐሳብ በመቃወም፤ በዋይት ሐውስ ደጃፍ በርካቶች ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ በተቃውሞ ሠልፉ ላይ “የፍልስጤም [መሬት] ለሽያጭ አይቀርብም” የሚለው መፈክር በሥፋት ተስተጋብቷል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞን ያሳተፈው ተቃውሞ የመጣው፤ በጋዛ ጥቃት ሠንዝረው ቢያንስ 47 ሺህ ንጹሐንን ያስገደሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንሚን ኔታንያሁ በትራምፕ ግብዣ ዋይት ሐውስ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ ሠልፈኞቹ ትራምፕን ከመቃወም ጎን ለጎን የአሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡

“ነጻነት ለፍልስጤም” ሲሉ የተደመጡት እነዚህ ተቃዋሚዎች፤ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው አስተያየቶችም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ያቀረቡትን ጋዛን የማጽዳት ዘመቻ ክፉኛ ተችተዋል፡፡ ከአልጀዚራ ጋር ቆይታ ያደረገው ሚካኤል ሺርዘር የተባለ የሠልፉ ተሳታፊ፤ “አሜሪካዊያን የምንከፍለው የግብር ገንዘብ ፍልስጤማዊያንን ለመግደል እንዲውል አንፈልግም” ብሏል፡፡ በትራምፕ የቀረበውን ጋዛን የማጽዳት ሐሳብም ውድቅ አድርጎታል፡፡

“የፍልስጤም ሕዝቦች የአገሬው ተወላጆች በመሆናቸው ወደየትም አይሄዱም” ያለው ሺርዘር፤ አስተሳሰቡን “ቅኝ ገዥነት የወለደው ነው ሲል” ነቀፌታ ሠንዝሮበታል፡፡ እንደ ሺርዘር ሁሉ የ24 ዓመት እድሜ ያላት ሶፊያ አሕመድ የተባለች ኢራናዊት፤ የፕሬዝዳንቱን ሐሳብ “አሳፋሪ ነው” ብላዋለች፡፡ ትራምፕ “ዘረኛ” መሆናቸውንም በመናገር፤ በሠልፉ ላይ የተገኘችው ይህን ለማጉላት መሆኑን አስረድታለች፡፡ በትራምፕ የተጋበዘው ኔታንሁም ቢሆን በዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት የሚፈለግ “ወንጀለኛ” መሆኑን አስታውሳለች፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሰልፉ የተካሔደባት የዋሺንግተን ዲሲ ግዛት “የወንጀለኞች መፈንጫ” መሆኗንም በመናገር፤ “ከሁሉም የከፋው ወንጀለኛ አሁን እዚህ ይገኛል” ብላለች፡፡  በዋይት ሐውስ ደጃፍ የተካሄደውን ሠልፍ ያስተባበረው የፍልስጤም ወጣቶች ንቅናቄ የተሠኘ ቡድን ነው፡፡ የቡድኑ ተወካይ ሙሐመድ ቃሲም፤ የሠልፉ ዋና ዓላማ “የጦር ወንጀለኛ” ሲል የጠራው ኔታንያሁ መምጣቱን መቃወም ነውመሆኑን ጠቁሟል፡፡ አያይዞም ትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎችን በማስገደድ ከቀያቸው የማፈናቀል ሥልጣን የላቸውም ሲል ሞግቷል፡፡

በተቃውሞ ሠልፉ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ ሀገራት የዘር ግንድ ያላቸው ግለሰቦች፣ ካነገቧቸው መፈክሮች መካከል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በጥብቅ በወንጀል የሚፈለግ በመሆኑ ለፍርድ እንዲቀርብ የሚጠይቀው ይገኝበታል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማጽዳት ዘመቻ በከፈቱባት ጋዛ፤ የተኩስ አቁም ትግበራውን ተከትሎ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ እንደሚገኝ ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የተመለሱት ቁጥራቸው ከ500 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ የጋዛ ተኩስ አቁም ትግበራ የመጀመሪያው ዙር ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር ንግግር እንደተጀመረ የፍልስጤሙ ሐማስ  ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዚህ ዙር የንንግሩ ማጠንጠኛ የሚሆነው የመጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ እና መልሶ ግንባታ ዙርያ እንደሚሆን የቡድኑ መግለጫ ላይ ሠፍሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular