የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ ለ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ከከተማዋ የተመዘገቡ ምዕመናን ቁጥር 320 መድረሱን ያስታወቀው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ መግለጫውን የሰጡት የምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ምዝገባው ከረመዳን ወር በፊት እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ጥር 28/2017 መግለጫውን የሰጠው በዋና ጸሐፊው ሸይኽ ሑሴን በሺር፣ በሥራ አስኪያጁ አቶ ሪያድ ጀማል እና የሐጅ እና ዑምራ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢስሓቅ ዓብዱልዓዚዝ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ በመግለጫው የሐጅ ምዝገባ ከተጀመረበት ጥር 15/2017 አንስቶ የነበረው ሒደት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ገደማ በአዲስ አበባ የተመዘገቡትን ምዕመናን ቁጥር ይፋ ሲያደርጉ፤ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ ጣቢያዎች የተመዝጋቢዎች ቁጥር 1 ሺሕ 200 መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች በዘንድሮው ዓመት ከኢትዮጵያ የሚሳተፉ ምዕመናንን ቁጥር በተመለከተ ከ“ሚንበር ቲቪ” ለቀረበላቸው ጥያቄ 10 ሺሕ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በዛሬው መግለጫ ለከተማው ምክር ቤትም ሆነ ለክልሎች ኮታ ባለመቀመጡ የተጠቀሰው ቁጥር መሙላቱ እስኪረጋገጥ ድረስ በሁሉም ጣቢያዎች ምዝገባ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት 12 ሺህ ምዕመናን ለሐጅ መጓዛቸውን ያስታወሱት ኃላፊዎቹ፤ ቁጥሩን ለመቀነስ ያስገደደው ሀገሪቱ ተግባራዊ ባደረገችው አዲስ የውጭ ምንዛሬ አሠራር መነሻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል በዛሬ መግለጫ ላይ፤ የምዝገባው ቀን መጨረሻ ሸዋል 30/1446 ዓ.ሂ (የካቲት 22/2017) እንደሚጠናቀቅ በማስታወስ፤ ቀጥሎ በሚመጣው የረመዳን ወር ምንም ዐይነት ምዝገባ እንደማይኖር ምዕመናን ማወቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ቀደም ብለው ማሥረጃዎችን በመያዝ እንዲመዘገቡ አሳስበዋል፡፡ ከተመዝጋቢዎቹ መካከል በራሳቸው ትኬት ቆርጠው መጓዝ ለሚፈልጉ ከሁለት በኋላ ምዝገባ እንደሚጀመር በማንሳት፤ የኢትዮጵያዊያን ፓስፖርት የሌላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የሚስተናገዱበት አሠራር በቀጣይ ቀናት ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ በባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ከሆነ፤ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ምዝገባ ለማከናወን የሚያስፈልገው ከዘጠኝ ወር በላይ ግዜ ያለው ፓስፖርት፣ የቀበሌ እና ፋዳን ጨምሮ ሌሎች ማንነትን የሚገልጹ መታወቂያዎች እንዲሁም መንጃ ፍቃድ ነው፡፡ ለሐጅ ምዝገባው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጁ የምዝገባ ጠቢያዎች ብዛት 30 መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቀደም ብሎ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒቴር ባወጣው ይፋዊ መረጃ ባለፈው ዓመት ከመላው ዓለም በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የተሳተፉ ምዕመናን ቁጥር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












