በማዕከላዊ ፈረንሣይ ሊዮን ከተማ የሚገኘው “አል ኪንዲ” የሙስሊም ትምሕርት ቤት በቀጣዩ የትምሕርት ዘመን የመዘጋት ሥጋት እንደተደቀነበት ተነግሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 የተመሠረተው ትምሕርት ቤቱ፤ የመዘጋት ሥጋት የተጋረጠበት በተያዘው ወር የሚገኝበት ጠቅላይ ግዛት የገባውን ውል በማቋረጡ ነው፡፡
ውሳኔውን ያሳለፉት ኃላፊዎች፤ “አቡ ዩሱፍ ያዕቁብ ኢብን ኢስሓቅ አስሰበህ አል ኪንዲ” በሚለው የመዝገብ ሥማቸው የሚታወቁትን ፋና ወጊ ሙስሊም ፈላስፋ ሥያሜ የተዋሰውን ትምሕርት ቤት ውል ለማቋረጣቸው፤ የትምሕርት አሰጣጥ ሒደት ላይ፣ አስተዳደራዊ ክፍተቶችን እንዲሁም “የሀገሪቱ እሴቶች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል” የሚል ውንጀላ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ አስረጂ ነው በሚል በትምሕርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በተደረገው ፍትሻ፤ ጽንፈኝነት ያራምዳሉ ያሏቸውን ሁለት መጻሕፍት አግኝተናል ማለታቸውንም ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ እነዚህ ጽፈኝነትን ያራምዳሉ የተባሉ መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ አልተጠቀሱም፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ የተባሉት መጻሕፍት ከእስልምና እና ሙስሊሞች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በትምሕርት ቤቱ ዩትዩብ ቻናል ላይ አንድ ፕሮፌሰር ከገላ ጋር የሚጣበቅ የሴቶች አለባበስ እና ሜክአፕ ሊታገድ ይገባል የሚል አስተያየት የሰጡበት ትምህርት መተላለፉንም በጽንፈኝነት መፈረጁን ዘገባው ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ግዛቱ ውሳኔውን የማያጥፍ ከሆነ 600 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ሙስሊም ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታ ውጪ ለመሆን ይገደዳሉ፤ አልያም ደግሞ በሌሎች እስላማዊ እሴታቸው ባልተጠበቁ ትምሕርት ቤቶች የመማር ግዴታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በፈረንሣይ ከአንድ ዓመት በፊት የኖርድ ጠቅላይ ግዛት ሌሎች አስተዳዳራዊ ምክንያቶችን በማቅረብ አቬሮስ የተሰኘ የሙስሊም ትምሕርት ቤት እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ በሊዮን በሚታተ አንድ ጋዜጣ ላይ አስተያየት ያሰፈሩት የሠራተኛ መደብ ካውንስል አባል የሆኑት ፈሪድ ቢንሙሳ፤ በፈረንሣይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከእነዚህ ሁለት ትምህርት ቤቶች ውጪ በአስተዳደራዊ ውሳኔ እግድ የተላለፈበት ሌላ ተቋም አለመኖሩን በመግለጽ፤ ውሳኔውን ተችተውታል፡፡ በእገዳው ላይ ምላሽ የሰጡት የአል ኪንዲ ትምሕርት ቤት ዳይሬክተር ዓብዱልወሃብ በኪ፤ የሚያስተዳድሩት ትምሕርት ቤት የሀገሪቱን እሴቶች ለመጠበቅ የሚሠራ መሆኑን በመግለጽ፤ እንደ ችግር የተጠቀሱት ጉዳዮችም ሊስተካከሉ የሚችሉና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡
በተያዘው ወር ኮንትራቱ የተቋረጠው አል ኪንዲ የሙስሊም ትምሕርት ቤት፤ ባኩሎሬት በተሠኘው የፈረንሳይ ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












