Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችአሕመድ አሸረዕ፣ ሙሐመድ ቢን ሰልማን እና የኤርዶጋን ግብዣ

አሕመድ አሸረዕ፣ ሙሐመድ ቢን ሰልማን እና የኤርዶጋን ግብዣ

ሶሪያ በሻር አል አሰድን ከሸኘች በኋላ የተተኩት የ43 ዓመቱ አሕመድ አሸረዕ፤ በይፋ የሀገሪቱ ቁጥር አንድ ሰው ከሆኑ ጥቂት ቀናት ተቆጠሩ፡፡ ሰውዬው የጊዜያዊ መንግሥቱ ፕሬዝዳንት ተደርገው የተሾሙት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቀናት፤ ደማስቆ የደረሱበት “ሐያት ተሕሪር አልሻም” የተሰኘው የታጠቀ ኃይል ተበትኖ በሀገሪቱ መደበኛ ጦር ውስጥ እንዲታቀፍ በመወሰን ነው፡፡ በይፋ የፕሬዝዳንት መንበር ላይ እንደተቀመጡ የኳታሩን አሚር ተሚም ቢን ሐማድን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ የኳታሩ አሚር ከጦርነት መልስ የመጀመሪያው የሶሪያን መሬት የረገጠ የውጪ ሀገር መሪ ሆነዋል፡፡

አሕመድ አሸረዕ የኳታሩን አሚር ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብለው ሲያናግሩ፤ ለእርሳቸው ደግሞ የመጀመሪያውን ይፋዊ የውጭ ሀገር ጉዞ ያደረጉት ግን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ነው፡፡ ትናንት እሑድ ወደተወለዱበት ሪያድ ከተማ ተጉዘዋል፡፡ በዚያም የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ተቀብለው የሀገሪቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ዘንድ አድርሰዋቸዋል፡፡

የሶሪያው ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ጉዟቸውን ወደ ሳዑዲ ሲያደርጉ፤ የወዳጅ መስመር እያበጁ መሆኑን በግልጽ ለማሳየት የፈጸሙት መሆኑን የጻፉ መገናኛ ብዙኃን በርካታ ናቸው፡፡ በርግጥ ሰውዬው ቀድሞ ከእነማን ጋር ይበልጥ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት እንደሚኖራቸው ፍንጭ የሰጡት፤ ለቃለ ምልልስ የኳታሩን “አልጀዚራ”ን በመተው ለሳዑዲ ዐረቢያው “አል ዐረቢያ” ቃለ ምልልስ ሲቀመጡ መሆኑን የተናገሩ ተንታኞች አሉ፡፡ በዚያን ወቅት የሶሪያ ቀጣይ ወዳጅ እንደ በሻር አል አሰድ አገዛዝ ዘመን ኢራን እና የባሕረ ሰላጤ ሀገራት ሳይሆኑ፤ ሳዑዲ ዐረቢያ እና ቱርክ እንደሚሆኑ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት ከቱርኩ “ኤ-ሔበር” ጋር በነበራቸው ቆይታም ይህን መከራከሪያ የሚያጠናክር ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚህ ቆይታቸው ወደ ውጪ ሀገራት መጓዝ ሲጀምሩ ‘በቀዳሚነት ቱርክ አልያም ሳዑዲ ዐረቢያን መጎብኘት እፈልጋለሁ’ ብለው ነበር፡፡ ቃላቸውን ጠብቀው ትናንት እሑድ ሪያድ ደርሰዋል፡፡ ከሪያድ አልፈው መካ ተሻግረው የዑምራ ሥነ ሥርዐት መከወናቸውን የሳዑዲ ዐረቢያ መገናኛ ብዙኃን አስነብበዋል፡፡

ዛሬ ሰኞ ከሰዓት የቱርክ መገናኛ ብዙኃን እንደጻፉት ደግሞ፤ ነገ ማክሰኞ ደግሞ ወደ አንካራ ይጓዛሉ፡፡ የአንካራው ጉዞ የመጣው የቱርኩን ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋንን ግብዣ ተከትሎ ነው፡፡ አሸረዕ በቱርኩ መገናኛ ብዙኃን “ሶሪያ መቼም ቢሆን ውለታቸውን አትረሳም” ያሏቸው ኤርዶጋን ሐያት ተሕሪር አሸም ደማስቆ ሲደርስ፤ ቀድመው በመደወል “እንኳን ደስ አለህ” እንዳሏቸው በማስታወስ ነበር፡፡ በእነዚህ የፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ የሀገራት ጉብኝት፤ በጦርነት የፈራረሰችው ሶሪያ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለመመለስ እየተጣጣረች ትገኛለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular