አዲሱ የሶሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ፤ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ሪያድ ከተማ በማቅናት ከልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ጋር የተወያዩት በዛሬው እለት ነው።
አሸረዕ ከሹመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጓዙባት ሳዑዲ ዐረቢያ፤ ሁለት ቀናት ይቆያሉ ተብሏል። መዲናዋ በደረሱበት ወቅት በሪያድ ምክትል ገዥ ልዑል ሙሐመድ ቢን ዐብዱረሕማን አቀባበል የተደረገላቸው ፕሬዝዳንቱ፤ ከሳዑዲ ዐረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ውይይት ያደረጉት ከሰዓት በኋላ መሆኑን በእንግድነት ያረፉበት ሀገር ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ወደ ሪያድ በረራ ሲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሰድ አሸባኒን አስከትለዋል። ከውይይቱ በኋላ የተናገሩት አሸረዕ፣ ከሙሐመድ ቢን ዛይድ ጋር የተደረገው ውይይት ሳዑዲ ዐረቢያ ለሶሪያ ቀጣይ ግንባታ እውነተኛ ፍላጎቷን ያሳየችበት ነበር ብለዋል። የውይይቱ ትኩረት የነበረው ኢነርጂ፣ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት እና የጤና ዘርፍ መሆኑንም ገልፀዋል።
በሳምንቱ አጋማሽ በይፋ የሶሪያ ፕሬዝዳንት ሹመት የተቀበሉት አሕመድ አሸረዕ፣ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ከመጓዛቸው አስቀድሞ በደማስቆ የኳታሩን አሚር መቀበላቸው ይታወሳል። ወደ ሪያድ ካደረጉት ጉዞ በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ በቀዳሚነት ለመጓዝ በእቅዳቸው ውስጥ ከተካተቱ ሀገራት መካከል ከሳዑዲ ዐረቢያ በተጨማሪ ቱርክን ጠቅሰዋል። (ሚንበር ቲቪ)












