Homeዜናና ወቅታዊዜናጠቅላይ ምክር ቤቱ ማንኛውም “ኢስላማዊ ስብሰባ” ከእውቅናው ውጭ እንዳይካሔድ ክልከላ ጣለ

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ማንኛውም “ኢስላማዊ ስብሰባ” ከእውቅናው ውጭ እንዳይካሔድ ክልከላ ጣለ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ማንኛውም “ኢስላማዊ ስብሰባ” ከእውቅናው ውጭ እንዳይካሔድ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይህንኑ ለሰላም ሚኒስቴር እና ለፌዴራል ፖሊስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕረሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ የካቲት 10/2017 በጻፉት ደብዳቤ ላይ ይህንኑ ገልጸዋል፡፡ ደብዳቤው እንደሚያመለክተው፤ ምክር ቤቱ ክልከላውን የጣለው “በቀጣይ ወራት” አካሔደዋለሁ ካለው ምርጫ ጋር በተገናኘ ነው፡፡

በሁሉም ክልል እና የከተማ አስተዳደር ከመስጂድ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ምርጫ ለማካሔድ ወደ ሥራ መግባቱን የሚገልጸው ደብዳቤው፤ ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች “ምርጫውን ለማደናቀፍና የሙስሊሙን አንድነት ለመሸርሸር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አንዳንድ የክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች መረጃ እንዳደረሱ” ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ድርጊቶች የተፈጸሙት በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሆነ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ ምርጫውን ለማደናቀፍና የሙስሊሙን አንድነት ለመሸርሸር ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት ግለሰቦች እና ቡድኖች “በስብሰባ፣ በሥመ ሙሐደራ፣ እና ኮንፍረንስ” ሥያሜ ይህን ድርጊት እንደሚፈጽሙ ጠቅሷል፡፡

“ሚንበር ቲቪ” ውሳኔውን በተመለከተ ያናገራቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባልደረባ፤ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ምርጫውን ተከትሎ “ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ” መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውሳኔው “አንደኛው ወገን ሌላኛውን እንዳይዘልፍ” ለመከላከል የተደረገ መሆኑን የሚያስረዱት ባልደረባው፤ ኢስላማዊ ስብሰባዎች በምክር ቤቱ ዕውቅና የሚደረጉ ከሆነ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን “ኃላፊነት የሚወስድ” አካል መኖሩን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከሆነ በቀጣይ የሚያካሔደው ምርጫ በመስጂድ የሚደረግ ነው፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ትናንት ማክሰኞ የካቲት 18/2017 በተጀመረው የዑለሞች ጉባዔ መርሐ ግብር ላይ ይህን አረጋግጠዋል፡፡ በምርጫው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተወካዮቹን በመስጂድ በመመረጥ ወደ ሌሎች መዋቅሮች እንደሚልክም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ፤ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት አመራሮች በተመረጡበት ሐምሌ 2014 የሰጣቸው የሥልጣን ጊዜ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ ይህ የሦስት ዓመት ጊዜ ሐምሌ 11/2017 አንደሚደፍን ያስታወሱት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት፤ ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ መካሄድ እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ ይከናወናል በተባለው ምርጫ የሚመረጠው አመራር፤ ተቋሙን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራ እንደሚሆን ከዚህ ቀደም ተገልጿል። ምክር ቤቱ ምርጫው በቀጣይ ወራት ይካሔዳል ከማለት ባሻገር እስካሁን ድረስ ትክክለኛ የጊዜ ሠሌዳውን ይፋ አላደረገም። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular