በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርንያ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት የሎስ አንጀለስን አንዳንድ አካባቢዎችን ወደ አመድነት የቀየረው ባለፈው ሳምንት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሰደድ እሳቱ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር እስከዛሬው ዕለት ድረስ 24 ደርሷል፡፡ የንብረት ውድመቱም ከ135-150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው በአካባቢው ቅዳሜ እና እሑድ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ንፋስ የነበረ ቢሆንም ሳንታ አና የተሰኘው ኃይለኛው ንፋስ ከትናንት እሑድ ምሽት ጀምሮ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ረቡዕ ድረስ እንደገና እንደሚነሳና በሰዓት 60 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አናዶሉ ኤጀንሲ ይዞት በወጣው የተጠናቀቀው እ.አ.አ የ2024 መረጃ፤ በመላው ዓለም በደረሱ አደጋዎች የደረሰው የንብረት ውድመት 320 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ከተመዘገቡ አደጋዎች መካከል 93 በመቶ የሚሆኑት ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ እነዚህ አደጋዎች ለ11 ሺሕ ገደማ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል፡፡
አደጋዎቹ የተመዘገቡባቸው ሀገራት አሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ካናዳ፣ ኮባ፣ ሆንዱራስ፣ ስፔን ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ጣሊያን፣ ኦስትሪያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ ታይላንድ፣ ሚያንማር፣ ፊሊፒንስ፣ ላኦስ እና ጃፓን ናቸው፡፡ የተመዘገቡት አደጋዎች ደግሞ ሰደድ እሳት፣ ማዕበል፣ አውሎ ንፋስ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንቀጥቀጥ መሆናቸው ተዘርዝሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












