የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ከሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር የዘንድሮውን ዓመት የሐጅ ጉዞን አስመልክቶ ስምምነት መፈራረሙን ያስታወቀው በዛሬው እለት ነው፡፡
ዛሬ ሰኞ ጥር 5/2017 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ጉዞን የተመለከተ የሁለትዮሽ መግባቢያ ሠነድ ተፈራርሟል፡፡
የመግባቢያ ሠነድ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንትና የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪ በሸይኽ ዓብዱልዓዚዝ ሸይኽ ዓብዱል ወሊ እና በሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅና ዑምራ ሚኒስትር ተውፊቅ ራቢዓ እንደተፈረመ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን የስምምነቱን ዝርዝር በተመለከተ የገለጸው ነገር የለም፡፡
የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪ የተመራ ልዑክ በሳዑዲ ዐረቢያ በተዘጋጀው የ1446 ዓ.ሂ ዓመታዊው የሐጅ ማስጀመሪያ አውደ ርዕይ ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ምክር ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በአውደ ርዕዩ ከሚቀርቡ ልምዶችን ከመቅሰም ጎን ለጎን ከአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋርም ተጨማሪ ስምምነቶች ይፈራረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃው አክሏል።
ምክር ቤቱ የዘንድሮ ዓመት የሐጅና ዑምራ ምዝገባ መርሐ ግብር በቅርብ ቀን ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ 12 ሺሕ ምዕመናን መጓዛቸው የሚታወስ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












