የጎረቤት ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ዛሬ ቅዳሜ ጥር 3/2017 ነው።
ሐሰን ሸይኽ አዲስ አበባ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች ከአንድ ወር በፊት በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን አማካኝነት ታኅሣሥ 2/2017 በአንካራ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ በወቅቱ በአንካራ በደረሱበት ስምምነት፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።
በቱርክ ይታገዛል የተባለው ውይይት በየካቲት ወር እንዲጀመር ከውሳኔ ተደርሷል። መደበኛው ስምምነት ደግሞ በአራት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር።
በሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት የኮንትራት፣ የኪራይና የመሳሰሉት የንግድ ስምምነቶች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል። (ሚንበር ቲቪ)












