ኦሳማ ቃሾን ይባላል፡፡ የ44 ዓመት እድሜ ያለው ፍልስጤማዊ ነው፡፡ እንደ አብዛኛው ፍልስጤማዊ የቀዬው ጉዳይ ያሳስበዋል፡፡ እንደ ሁሉም ፍልስጤማዊ ደግሞ ገና በአፍላ ዘመኑ ለታጋይነት የታጨ ነው፡፡ በፍልስጤም ሳለ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የሚታጣ ሰው አልነበረም፡፡ ለፍልስጤም ሲሟገት እንደ አብዛኛው የሀገሩ ሰው እስር እና ድብደባ አስተናግዷል፡፡ በዚያ ለመቆየት የቻለው ግን እ.አ.አ አቆጣጠር እስከ 2003 ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ለመጨረሻ ጊዜ እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የተካሄደ አንድ የተቃውሞ ሠልፍ ካስተባበረ በኋላ መቆየት አስጊ ስለሆነበት ወደ ስደት ሀገር ማቅናት መረጠ፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኦሳማ የስደት እግር የጣለው ወደ አውሮፓ ነበር፡፡ ወደ አሕጉሩ ተሻግሮ አሁን የሚኖረው በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ለንደን ደርሶም ቢሆን ጧት ማታ የሚብከነከነው ስለ ፍልስጤም እና ፍልስጤማዊያን ነው፡፡ በ2010 ነጻ የጋዛ እንቅስቃሴ የተሠኘ የመብት ተሟጋች ድርጅት በመመሥረት ስለ ፍልስጤም መታገል ቀጠለ፡፡ በድርጅቱ በኩል ወደ ጋዛ ሰብዓዊ ርዳታ በሚላክበት መንገድ ላይ ሲሠራ ቀይቷል፡፡ ኦሳማ መልከ ብዙ ነው፤ ፊልም ይሠራል፤ ዘጋቢ ፊልም ሲሠራ ይዋጣለታል የሚባል ነው፡፡ ፊልም ብቻ ሳይሆን ሲነግድም የሚዋጣለት ነው፡፡ በለንደን ንግድ ላይ ቢሰማራ ፍልስጤምን ማሰቡ አይቀርም፡፡ ሥያሜውን ከፍልስጤም ጋር የሚተሳሰርበትን መንገድ ይፈልጋል።
ኦሳማ ቃሾ ሲነግድ ትርፉን ለፍልስጤማዊያን እንዲደርስ የሚያደርግም ነው፡፡ ይህን አላማ ከሚያሳካባቸው ንግዶች መካከል አንደኛው የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ሆኗል፡፡ “ጋዛ ኮላ” የኦሳማ ቃሾ የስላሳ መጠጥ ምርት ነው፡፡ ፍልስጤማዊው ጋዛ ኮላን ማምረት የጀመረው እንዲሁ ለነጋዴነት አምሮት ብቻ አይደለም፡፡ ለለስላሳ መጠጥ ምርቱ ሥያሜውን በተዋሰው ጋዛ ከተማ በእስራኤል ወታደሮች የሚደርሰውን የሰብዓዊ እልቂት በመደገፍ ሥሙ የሚነሳውን “ኮካ ኮላ”ን ለመተካት በማሰብ ነው፡፡
ለእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ የለስላሳ መጠጥ አፍቃሪ አለመሆኑን የሚናገረው ኦሳማ፤ እሱ ባይወደውም ሰዎች “የለስላሳ መጠጥ መጠቀማቸው ካልቀረ ግን በኮካ ኮላ ፋንታ ለምን ጋዛ ኮላን አይጠጡም?” በሚል ሐሳብ እንዳስጀመረው ያስረዳል፡፡ ከለስላሳ መጠጡ የሚገኘው ትርፍ ደግሞ በፍልስጤም ለወደመው አልካርማ ሆስፒታል ጥገና የሚውል ነው፡፡ ለጥገና ገንዘብ የሚያሰባስብለት አል ካርማ ሆስፒታል የወደመው በእስራኤል ወታደሮች ነው፡፡
አሁን እሱ ገንዘብ የሚያሰባስብለትን ሆስፒታል የእስራኤል ወታደሮች “ለምን እንዳወደሙት ምንም አይገባኝም” የሚለው ኦሳማ፤ “ግን ደግሞ ሌሎቹን የጋዛ መሠረተ ልማቶችም ለምን እንዳወደሟቸው ምን የተለየ ምክንያት አላቸው?” ሲል በግራ መጋባት የራሱ ጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ይሰነዝራል፡፡ ነገር ግን ሆስፒታሎቹ ሲወድሙ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አልፈለገም፡፡ ምንም እንኳን እኔ የማደርገው ትንሽ ቢሆንም መነሳት አለብኝ ብሎ ጋዛ ኮላን ማምረት ጀመረ፡፡ ይህን ለምን እንዳደረገ ሲጠየቅ፦ “የምንሠራው ትንሽ ቢሆንም እስከፈለግነው ማለም ተፈቅዶልናል፤ ራዕይ ሊኖረን ይገባል፤ ካልሆነ እንዴት መኖራችን ማረጋገጥ እንችላለን?” ሲል መልሷል፡፡
የኦሳማ ቃሾ ጋዛ ኮላ ፍልስጤምን በሚወክሉ ቀለማት የተዋበ ነው፡፡ ምርቱ ወደ ተጠቃሚዎች መድረስ ከጀመረበት የፈረንጆቹ 2023 አንስቶ እስካሁን ድረስ 500 ሺሕ ጠርሙስ መሸጥ ችሏል፡፡ ይህ የሚሆነው በኦንላይን አማራጮች ነው፡፡ በለንደን 24 ጠርሙስ የሚይዘው አንድ እሽግ የጋዛ ኮላ ላስላሳ መጠጥ በ30 ፓውንድ ይሸጣል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ምርቱ ከእንግሊዟ ለንደን ተሻግሮ ወደ ስፔን፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኩዌት ደርሷል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በጋዛ እና ዌስት ባንክ የሚገኙ የቃሾ ዘመዶች እና ጓደኞቹም ጭምር ገዛ ኮላን እስካሁን አልቀመሱትም፡፡ ሆኖም ከምርቱ ሽያጭ በሚገኘው ትርፍ በተገነባው ሆስፒታል ትሩፋቱን መቋደሳቸው አይቀርም።
ባለፉት ጊዜያት በፍልስጤም ምድር ለሚፈጸመው ግፍ በይፋ ጦር በማቀበል ከሚደግፉት በተጨማሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እስራኤልን የሚደግፉ የግፈኛ በትር አቀባዮችን ለመቅጣት የሚደረገው ትግልም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደቀጠለ ነው፡፡
በፍልስጤማዊያን የሕልውና ትግል ውስጥ እንደ ኦሳማ ሁሉ በስዊድን ማልሞ ነዋሪ የሆኑት የሑሱን ቤተሰቦችም ከዚህ ቀደም ኮካ ኮላን የሚተካ ለስላሳ መጠጥ አስተዋውቀዋል፡፡ እነ ኦሳማም ሆነ የሑሱን ቤተሰቦች እየተፋለሙ የሚገኙት በቀጥታም ይሁን እስራኤልን የሚደግፉ የግፈኛ በትር አቀባዮችን ነው፡፡ በትር አቀባዮቹ ስለ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት እቆረቆራለሁ የምትለው አሜሪካ ዐይነቶቹ ብቻ አይደሉም፡፡ እነ ኮካ ኮካ ኮላ ብቻም አይደሉም፡፡ ማክዶናልድ እና ስታርባክስም አሉበት፡፡ በርግጥ እነዚህ ሁሉም በጓሮ በኩል ሥራቸውን እየቀጠሉ በአደባባይ እኛ የለንበትም ብለው መከራከራቸው አልቀረም፡፡ እነርሱ ይህን ቢሉም ፍልስጤማዊያኑ የሐሰት ማስተባበያውን የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ ለዚህም እስከ ነጻነት ድረስ በተጋድሏቸው ቀጥለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












