የዓለም አቀፍ ሙስሊም ምሑራን በግብጽ ሀገር የሚገኘው እንደ አል-አዝሐር ዩኒቨርሲቲ ያሉ የሙስሊም ዓለም ተቋማት ፍልስጤማዊያንን ከእስራኤል ወረራ እና ከተደቀነባቸው ረሐብ እንዲታደጉ የዓለም አቀፍ ሙስሊም ምሑራን ኅብረት ጥሪ አቀረበ፡፡ ኅብረቱ በመግለጫው “የእስላማዊ ትብብር ሀገራት ድርጅት”ን እና “ዐረብ ሊግ”ንም በሥም በመጥቀስ ከጋዛ ንጹሐን ጎን እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡
የኅብረቱ ጥሪ የቀረበው በዋና ጸሐፊው ዶክተር ዓሊ ሙሐመድ አልሶላቢ በኩል ነው፡፡ በመግለጫው ዶክተር ዓሊ አልሶላቢ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ፊት አውራሪነት በመሣሪያ እና ዲፕሎማሲ የኃይል ሚዛን የተደራጁ ሀገራት የእስራኤልን ወረራ መደገፋቸውን በማንሳት ትችት ሰንዝረዋል፡፡ አያይዘውም እነዚህ ሀገራት ከእስራኤል ጎን በመሰለፋቸው ፍልስጤማዊያንን የመታደግ ኃላፊነት ከአል አዝሐር ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በእስላማዊ ትብብር ድርጅትን እና ዐረብ ሊግ ሀገራት ትከሻ ላይ መውደቁን አስታውሰዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ድርጅቶች ከሚታቀፉ ሙስሊም እና ዐረብ ሀገራት በተጨማሪ የገልፍ ትብብር ምክር ቤት በተመሣሣይ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ አስሶላቢ በዚሁ መግለጫ ላይ ሦስቱ ድርጅቶች የጋዛን ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳ ሊያደርጉ እንደሚገባ የወተወቱ ሲሆን፣ የፍልስጤም ቀውስ የገልፍ ሀገራት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ቀላል አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በኅብረት መግለጫ ላይ የተጨቆኑትን መደገፍ የእስልምና መሠረታዊ መርሕ መሆኑን አፅንዖት በመስጠት፤ መላው የሙስሊሙ ዓለም ከተጨቆኑት ጎን እንዲቆሙ እና መብታቸውን በሁሉም ሕጋዊ መንገዶች ማስጠበቅ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡
አክለውም “ወንጀለኛ” ሲሉ የጠሯቸው የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ ውስጥ የሚገኙ እንደ ትምሕርት ቤት፣ ሆስፒታል እና የመንግሥት ተቋማትን እንዲሁም የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ማውደማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ሙስሊም ምሑራን ፍልስጤማዊያንን እንዲታደግ ጥሪ የቀረበለት በግብጽ ካይሮ የሚገኘው አል-አዝሐር ዩኒቨርሲቲ፤ በሙስሊሙ ዓለም የሃይማኖት ትምሕርት ማዕከልነት የሚታወቅ ነው፡፡

ዶክተር ዓሊ ሙሐመድ አልሶላቢ በዋና ጸሐፊነት የሚያገለግሉበት ዓለም አቀፍ የሙስሊም ምሑራን ኅብረት የተመሠረተው እ.አ.አ በ2004 ነው፡፡ ዋና መቀመጫውን በኳታር እና አየርላንድ ደብሊን ያደረገውን ኅብረት በመሥራችነት የሚጠቀሱት፤ ከሁለት ዓመት ወደ አኺራ የተሻገሩት ግብጻዊው ሸይኽ ዩሱፍ አል ቀርዷዊ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












