Homeዜናና ወቅታዊዜናከበሻር አል አሰድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ የመጀመርያው የአውሮፕላን በረራ ወደ ደማስቆ ተደረገ

ከበሻር አል አሰድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ የመጀመርያው የአውሮፕላን በረራ ወደ ደማስቆ ተደረገ

በሶሪያ የበሻር አል አሰድ አገዛዝ ወድቆ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ወደ ሞስኮ ከኮበለሉ በኋላ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ በረራ ወደ ደማስቆ ተደርጓል፡፡ ትናንት ማክሰኞ በረራው ሲጀመር ሁለት አውሮፕላኖች ወደ ከተማዋ በረራ አከናውናዋል፡፡ ከበረራዎቹ መካከል ከኳታር የተነሳው ይገኝበታል፡፡

 በዮርዳኖስ መንግሥት የሚተዳደረው ፔትራ የዜና ወኪል እንደዘገበው ደግሞ፤ የሮያል ዮርዳኖስ አየር መንገድ አውሮፕላንም ወደ ደማስቆ የሙከራ በረራ አድርጓል፡፡ የሶሪያ ሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ኃላፊዎች እንደገለጹት፤ አውሮፕላኑ ወደ ደማስቆ ያመራው መደበኛ በረራዎች ከመጀመራቸው አስቀድሞ የከተማዋን አየር ማረፊያ ቴክኒካዊ ሁኔታ መገምገም አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

የሶሪያ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊ አሻድ አል ሱሌቢ እንዳሉት፤ ኳታር በእስራኤል የአየር ድብደባ እንዲሁም ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ ምክንያት ጉዳት ያስተናገደው አውሮፕላን ማረፊያ እንዲታደስ ድጋፍ አድርጋለች። ከተሳፋሪዎቹ መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው ከአስር ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራቸው የተመለሱ የሶሪያ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

አልጀዚራ ያናገራቸው ከዩናይትድ ስቴትስ የተመለሱት ኦሳማ ሙስለማ፤ በሀገራቸው እ.አ.አ በ2011 የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል። “ወደ ሀገራችን አንመለስም ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር” ያሉት ኦሳማ፤ “አላህ ፈቅዶ ሶሪያ ዳግም በዜጎቿ እጅ ወድቃለች” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል፡፡ የደማስቆ አውሮፕላን ማረፊያ በረራዎችን ማስተናገድ የጀመረው ከ13 ዓመታት በኋላ ነው፡፡

በሶሪያ ሐያት ታህሪር አል ሻም የተሰኘው ቡድን ከአንድ ወር በፊት የአሳድን አገዛዝ ከሥልጣን መገርሰሱን ተከትሎ ከቀድሞው መንግሥት ጋር ግንኙነታቸውን ያቋረጡ የዐረብ እና የምዕራባውያን ሀገራት ዳግም እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡

የሶሪያ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል ሺባኒ ባለፉት ቀናት ወደ ኳታር እና ሳዑዲ ዐረቢያ ተጉዘዋል። ሚኒስትሩ የጎበኟቸው ሀገራት በእርስ በእርስ ጦርነት ውድመት ያስተናገደችው ሶሪያን በመገንባት ረገድ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular