Homeዜናና ወቅታዊዜናየክልል እስልምና ጉዳዮች ም/ቤቶች በአክሱም በሙስሊም ሴት ተማሪዎች የተፈፀመውን የመብት ጥሰት አወገዙ

የክልል እስልምና ጉዳዮች ም/ቤቶች በአክሱም በሙስሊም ሴት ተማሪዎች የተፈፀመውን የመብት ጥሰት አወገዙ

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባ አንድ ሳምንት ብቻ ቢቀረውም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ምዝገባውን ማከናወን አልቻሉም

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የተፈጸመውን የሙስሊም ሴት ተማሪዎች የመብት ጥሰት የክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች አውግዘውታል። ምክር ቤቶቹ የተፈፀመው ድርጊት በሕዝብ መካከል መቃቃር የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

በአክሱም ከተማ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች የተፈፀመውን የመብት ጥሰት ካወገዙት መካከል የአፋር ክልል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች ይገኙበታል።

በተናጠል ባወጡት መግለጫ ሁሉም ምክር ቤቶች በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተፈፀመው ጥሰት ሕገ ወጥ መሆኑን በመግለጽ እልባት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

ምክር ቤቶቹ መግለጫ እንዲያወጡ ያስገደደው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ከትምሕርት ገበታ ውጪ መደረጋቸው ነው። በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለዋል የተባሉት “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት”፣ “አሉሚናይ”፣ “ወርኣይ”፣ “ክንደያ” እና “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” ናቸው፡፡

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ታኅሣሥ 25/2017 በሰጠው መግለጫ፤ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተጣለው የሒጃብ ክልከላ በሦስት ቀናት ውስጥ እልባት የማይሰጠው ከሆነ ወደ ቀጣይ ርምጃ እንደሚሻገር ማስጠንቀቂያ የሰጠ ቢሆንም እስካሁን ድረስ መፍትሔ አላገኘም።

በትምሕርት ቤቶቹ በተጣለው የሒጃብ ክልከላ ምክንያት ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚዘጋጁ ተማሪዎች እስካሁን ድረስ የተፈታኝ ቅጽ መሙላት እንዳልቻሉ ታውቋል። የትምሕርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባ ሊጠናቀቅ የቀረው አንድ ሳምንት ብቻ ነው።

በዚህም አገልግሎቱ ተማሪዎች ምዝገባውን ከጥር 6/2017 አስቀድሞ እንዲያጠናቅቁ ማሳሰቢያ የሰጠ ቢሆንም በአክሱም የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች እስካሁን ምዝገባውን ማካሔድ አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular