የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በክልሉ አክሱም ከተማ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተጣለው የሒጃብ ክልከላ በሦስት ቀናት ውስጥ እልባት የማይሰጠው ከሆነ ወደ ቀጣይ ርምጃ እንደሚሻገር አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው በዛሬው እለት በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
በመቐለ ከተማ ዛሬ ጁመዓ ታኅሣሥ 25/2017 ረፋድ ላይ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ 11 ነጥቦች የተካተተበት የክልሉ ምክር ቤት ወቅታዊ አቋም የተንጸባረቀበት ነው፡፡ የምክር ቤቱ መግለጫ የመጣው በተያዘው ሳምንት የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ በሒጃብ ጉዳይ አዲስ ክልከላ እንደማይቀበል በመግለጽ በነባሩ አሠራር እንዲቀጥል ትዕዛዝ ቢያሳልፍም ትምሕርት ቤቶቹ ውሳኔውን በመጣስ ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው ወደ ግቢ እንዳይገቡ ከከለከሉ በኋላ ነው፡፡
በመግለጫው ላይ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በቀዳሚነት በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላ ከተጣለ በኋላ የወረዳው እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በተዋረድ እስከ ክልል ድረስ ደብዳቤ መጻፉን አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ለደብዳቤው የተሰጠው ምላሽ አዎንታዊ አለመሆኑን በመግለጽ፤ ውሳኔው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት፣ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን፣ ትምሕርት ሚኒስቴር ደንቦች እና በክልሉ በሥራ ላይ የሚገኙ ሕግጋት የጣሰ ነው ብሎታል፡፡
በዚሁ መግለጫ በክልሉ ሃይማኖትን መሠረት ላደረገ “ቀውስ በር መክፈት” አስፈላጊ አለመሆኑንም በመጥቀስ ይህን የሚደረግ ከሆነ ከፍተኛ አደጋ የሚደቅን እንደሚሆን በመጠቆም ስጋቱን ገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩ “ሳይረፍድ በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው” ጠይቋል፡፡
የትምሕርት ሚኒስቴር ለሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚሠራ የአለባበስ ደንብ ካወጣ መቆየቱን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች መብታቸውን ተከብሮ በአስቸኳይ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ የተጠየቀበት ነው፡፡ አክሎም ከትምሕርት ሚኒስቴር መመሪያ ውጪ ሒጃብ እና ትምሕርት በመከልከል በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተለያየ ጉዳት ያደረሱ የትምሕርት ቤት አመራሮች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባም አሥፍሯል፡፡
በአክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጪ የሆኑት ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ነው፡፡ በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት”፣ “አሉሚናይ”፣ “ወርኣይ”፣ “ክንደያ” እና “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” መሆናቸውም ታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












