Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮች‘አዛን ከቢላል ጀምሮ ሲስተጋባ የነበረ ነው፤ በጥሪው የሚረበሹ ካሉ ጥለው መሔድ ይችላሉ’

‘አዛን ከቢላል ጀምሮ ሲስተጋባ የነበረ ነው፤ በጥሪው የሚረበሹ ካሉ ጥለው መሔድ ይችላሉ’

ፅንፈኛው ቀኝ ዘመም የእስራኤል የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ባለፈው እሑድ መስጂዶች የሚያሰሙት አዛን እንዲታገድ ውሳኔ መተላለፉን ከገለጸ በኋላ የሚሰማው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ሚኒስትሩ ለእገዳው የሰጠው ሰበብ “አይሑድ ነዋሪዎች እንዳይረበሹ” የሚል ነው።

ይህ እገዳ ከተሠማ በኋላ ተቃውሟቸው ካሰሙት መካከል የአሜሪካው የሙስሊሞች መብት ተሟጋቹ ‘ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ’ ይገኝበታል። ተቃውሞው ቀጥሎ በዛሬው እለት ደግሞ በመስጂደል አቅሷ ዳዕዋ በማድረግ የሚታወቁት ሸይኽ ኢክሪማ ሰብሪ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሸይኽ ኢክሪማ ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ በአዛን ጥሪ ድምጽ የሚረበሽ ካለ ጥሎ መሔድ ይችላል ሲሉ ውሳኔውን አጣጥለውታል። “ከመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ሙዓዚን ቢላል ቢን ረባህ ጊዜ ጀምሮ የአዛን ድምጽ በፍልስጤም ሰማያት ሲስተጋባ ነበር” ያሉት ሸይኽ ኢክሪማ፣ “ወደፊትም አይቆምም፣ በዚህ የሚረበሹ ካሉ ጥለው መሔድ ይችላል” ብለዋል።

አክለውም “የአዛን ጥሪ ከሰላት ጋር ቁርኝት ያለው ግዴታ ከሆኑ የኢስላም ሥርዐቶች ውስጥ አንደኛው ነው። ማንም ሊከለክለው አይችልም። ጥሪው ከሚናራዎች እንዳይወጣ ቢከለከል ከመኖሪያ ቤቶች ጣሪያ መነሳቱ አይቀርም” ሲሉ በክልከላ መቆም የሚችል ጉዳይ እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በፍልስጤም ሰማያት ላይ የሚስተጋባው የአዛን ጥሪ እስከ ዕለተ ቂያማ ድረስ ያለ ከልካይ መስተጋባቱን እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የአዛን ድምጽ እንዳይሰማ ክልከላ ለማድረግ ሲሞክሩ ይህ ለመጀመሪያ አለመሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል። ፅንፈኛው ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ ኢታማር ቤን ግቪር በ2016 አዛን እንዲከለከል ለሚጠይቅ አዋጅ ሲሟገት እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular