ከጋዛ ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቀው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን የጋዛ ቢሮ ኃላፊ ዋኢል ደህዱህ የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የ2014 “የጀግንነት” ሽልማት ማሸነፍ ችሏል። የጋዜጠኛው አሸናፊነት ይፋ የተደረገው ትናንት ምሽት በአሜሪካ ዋሺንግተን በተካሔደ መርሐ ግብር ላይ ነው።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ በዓለም ዙሪያ “የፕሬስ ነጻነትን ለመከላከል እና ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ” ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች እውቅና በሚሰጥበት መድረክ፣ ዋኢል አሸናፊ የሆነው “በጋዛ በደረሰበት ጉዳት እና በቤተሰቦቹ ሞት ሳቢያ ዘገባውን ማሠራጨቱን አቋርጦ ባለማወቁ” መሆኑን ጠቅሷል።
በሽልማት መርሐ ግብሩ ላይ መገኘት ያልቻለው ጋዜጠኛ ዋኢል ዳህዱህ፣ በመድረኩ ላይ በድምጽ የተቀዳ መልዕክት አስተላልፏል። “በጦርነት ወቅት ከጋዛ የምናገኛቸው ዜናዎች እና ምሥሎች ወደ ቀሪው ዓለም መድረሳቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለናል” ያለው ጋዜጠኛው፣ “ለዚህም ከፍተኛ ድካም፣ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ላብ እና ደም ጭምር ከፍለናል” ብሏል።
ከፍልስጤም ጋዛ ዘገባዎችን የሚያቀርበው ዋኢል ደህዱህ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተመሣሣይ ናሽናል ፕረስ ክለብ ያዘጋጀውን ሽልማት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ፍልስጤማዊው ጋዜጠኛ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከከፈተች በኋላ ባሉ ጥቂት ሳምንታት በቀጥታ ዘገባ ላይ ሳለ በኑሰይራት የስደተኞች ካምፕ ላይ የተፈጸመው በአየር ጥቃት ባለቤቱን፣ የሰባት ዓመት ሴት ልጁንና የ15 ዓመት ልጁን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰቡን አባላት እንደገደለ የተነገረው ነው፡፡
ዳህዱህ በታኅሣሥ ወር የአልጀዚራ ዘጋቢዎች ቡድን በተፈናቃይ ፍልስጤማውያን መጠለያ ትምሕርት ቤት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመሸፈን ሲሞክር ሲዘግብ ጉዳት አስተናግዷል፡፡ የ54 ዓመት ዕድሜ ያለው ዋኢል ሐማዳን ኢብራሂም ዱህዱህ፤ ጋዜጠኝነትን የጀመረው አል ቁድስ በተሰኘ ጋዜጣ ገና በ18 ዓመቱ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












