ሙሐመድ ኢድሪስ ካሣ የቴሌቪዥን ተመልካቾች በሚያቀርበው ተወዳጅ መሰናዶ ያውቁታል። ከዚያ ባሻገር ገጣሚ ነው። ለሙንሺዶች በሰጣቸው ግጥሞች አድናቆት የተቸረው። በዚህ ሳምንት በአዲስ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ መምጣቱን ይፋ በማድረግ ለግጥም ወዳጆች ለምርቃቱ ደግሦ ዛሬ (ቅዳሜ ኅዳር 21/2017) ከሰዓት እንዲታደሙ ጋብዟል። ሙሐመድ ከመጽሐፍ ምርቃቱ ሰዓታት አስቀድሞ ከ“ሚንበር ቲቪ” ድረ ገጽ ጋር በጣም አጭር ቆይታ አድርጓል።
ሚንበር ቲቪ፡- አሚን አሚንዬ እንዴት ያለ የግጥም መድበል ነው? ለኅትመት በቅቶ አንባቢ ጋር ሲደርስ ምን ስሜት ፈጠረብህ? የመገላገል ነው? (እፎይ የማለት) ወይስ ሌላ…
ሙሐመድ ኢድሪስ፡- ከ80 በላይ የሚሆኑ ከጉርምስና ዕድሜዬ ጀምሮ የተጻፉ ግጥሞች ናቸው። አንዳንዶቹ ከዚያም [ዕድሜ] አነስ ያሉ ናቸው። በ112 ገጾች ውስጥ ተሰብስበዋል። [መጽሐፉ ሲታተም] ድብልቅልቅ ስሜት ነው የተሰማኝ። በአንድ በኩል ደስ ብሎኛል፣ በሌላ በኩል ተዳፈርኩ እንዴ? ብያለሁ። የሆነ ሰዓት ላይ ደግሞ ምንም ትርጉም ያጣብኛል። የምሬን እኮ ነው! በቃ ይሄ ይሄ ነው ስሜቱ።
ሚንበር ቲቪ፡- ስለአንተ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች ‘ምናባዊና ቃላት የሚታዘዙለት ገጣሚ ነው’- ይሉሃል፡፡ አንተ እሱን አገላለጽ ትጋራዋለህ? የቃላት ሐብትህ ምንጩ የት ነው? በግልህ ምን ዓይነት ግጥሞች ነው የምትወደው?
ሙሐመድ ኢድሪስ፡- የሰዎችን ምሥክርነት ለማረም ወይም ለማስረገጥ ሥልጣኑ ያለኝ አይመስለኝም። ግን ከቃላት ጋር የተለየ ትስስር አለኝ። ቃላትን በስሜት ደረጃ፣ በሰማኋቸው ሁኔታ፣ ቦታ እና መንፈሥ ውስጥ ነው የምተዋወቃቸው። ስለዚህ እያንዳንዱ ነገር ውስጥ የምሰማቸው ቃላት በተለየ ቅንጅት ነው ትዝታዬ ውስጥ የሚነግሡት። መድረሳ የሰማኋቸው፣ ከነሺዳ የሰማኋቸው፣ ከመጽሐፍ ያነበብኳቸው፣ እናቴ ከነገረችኝ ተረት፣ አባቴ ካንጎራጎረልኝ የሆነ ስንኝ… ብቻ እንዲህ ነው በማልለው ሌሎችም አጋጣሚዎች ውስጥ ቃላትን እተዋወቃቸውና ግጥም ሆነው ያገለግሉኛል። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ቃላትን ከተፈጥሯቸውና ትርጓሜያቸው በተለየ መልኩ ሁሉ እረዳቸዋለሁ። ግጥሞች ከነፍስ ከኾኑ የምር ከኾኑ፤ በዛ ውበት ካላቸውና ካማሩ እወዳለሁ፡፡
ሚንበር ቲቪ፡- በግጥም መድበል ከመምጣትህ አስቀድሞ በነሺዳ ግጥሞች ትታወቃለህ…ሙስሊም ገጣሚ [በዚህ መልኩ መፈረጅ አከራካሪ ሊሆን ቢችልም] ስለ ግጥም ሲያስብ የሚያስጨንቀው ምንድን ነው? መንፈሣዊ ይዘት ላላቸው ግጥሞች ከይዘት ባሻገር ቅርጽ ቦታ አለው?
ሙሐመድ ኢድሪስ፡- እንደ አንድ ሙስሊም ሃይማኖታዊ ያልሆነውም ሕይወት የሚመራበት ሸሪዓዊ መስመር ይኖራል። እሱ ለአንድ ሙስሊም የተለየ ኪናዊ ልማድ እንዲያዳብር ያስገድደዋል። መጠበቅ ያለባቸው መለኮታዊ ድንበሮች ይኖራሉ። በማንኛውም ሞያ ውስጥ ላለ ሙስሊም ግለሰብ ይሄ ተጠባቂ ጉዳይ ይመስለኛል። ቃላትና ሐሳቦች ደግሞ ጥልቅ መሠረት ካላቸው ሸሪዓዊ ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ሊጋጩ የሚችሉበት ዕድል አይጠፋም። እሱን ማረቅ ሊያስፈልግ ይችላል። ያም እየሆነ ግን እንደ አንድ ሰው ደግሞ የሚሰሙ ተለዋዋጭና መልከ ብዙ ስሜቶች ከሚሠራው ኪናዊ (ጥበባዊ) ሥራ ጋር አብረው የሚፈሱ ናቸው።
ቅርጽን በምን ያህል ተመሳሳይ መንገድ እንደተረዳነው ርግጠኛ ባልሆንም፣ በእኔ ዕይታ የቅርጹ ውበትና ሥምረት ይዘቱንም በጥልቀት ለመግለጽ አቅም ይሰጣል፤ በተቃራኒውም ሊሆን ይችላል። ግጥም ወይም ሌላ የጥበብ ሥራ በውበትም በቅርጽም በይዘት ተሰናስሎ መስመር ይኖርበታል።

ሚንበር ቲቪ፡- በአዲሱ መድበል ልትሰጠን የሞከርነው ምንድን ነው?
ሙሐመድ ኢድሪስ፡-. . . ልጅነቴን።
ሚንበር ቲቪ፡- የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ፋይዳ ጥያቄ የሚነሳበት ባይሆንም በዚህ ዘመን አንድ ሰው ግጥም ሲጽፍና ሲያሳትም ከደስታው/ርካታው በስተቀር ምን ሊያተርፍ ይችላል? ደስታ/ርካታ ከእንጀራ ጋር የሚስማሙት በየት በኩል ነው? እሱን አንተ በምን ልትደፍነው ሞከርክ?
ሙሐመድ ኢድሪስ፡- የሃገሩም ሁኔታ ተጨምሮበት በሥነ ጽሑፍም ሆነ ሥነ ግጥም ሕይወትን መግፋት የሚታሰብ ነገር አይደለም። አስቦ የተነሳም ይኖራል ብዬ አልገምትም። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ከሥነ ግጥም ጋር የፈጠርኩት ውሕደትና ፍቅር እዚህ ድረስ አመጣኝ እንጂ፣ እንጀራዬ ይሆናል ብዬ ያሰብኩበት ጊዜ ብዙ አይመስለኝም። በተወሰነ ደረጃ ደግሞ እንጀራዬን አልሰጠኝም ብዬ አልደመድምም። በሚዲያ ሥራ ውስጥ ራሴን ያገኘሁት በሥነ ግጥም ላይ የነበረኝ መጠመድ ይመስለኛል። በቀጥታም ሊሆን ይችላል፣ አልያም በእጅ አዙር…
ሚንበር ቲቪ፡- የግጥም መድበልህ ዛሬ ይመረቃል። ምን ተዘጋጅቷል?
ሙሐመድ ኢድሪስ፡- የግጥም መጽሐፌ ዛሬ ኅዳር 21/2017 4 ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋሊያ መጽሐፍት ነው የሚመረቀው። በተለይ የዘመን እኩዮቼ ናቸው መድረኩ ላይ የሚኖሩት። ከዚያም ባሻገር ደግሞ ልጅነታችንን እያስታወስን የምንጨዋወትበት ነው የሚሆነው – አላህ ቢል።
ሚንበር ቲቪ፡- እናመሠግናለን፡፡












