Homeዜናና ወቅታዊዜናየሸሪዓ ፍርድ ቤቶች “ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ እና ከካፒታል ማርኬት ጋር የሚነሱ አለመግባባቶችን” የመዳኘት...

የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች “ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ እና ከካፒታል ማርኬት ጋር የሚነሱ አለመግባባቶችን” የመዳኘት ሥልጣን እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ የጥናት ሠነድ ላይ ውይይት ተካሔደ

የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች “ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ እና ከካፒታል ማርኬት ጋር የሚነሱ አለመግባባቶችን” የመዳኘት ሥልጣን እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ የጥናት ሠነድ ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ውይይት ተካሔዷል፡፡ ሰነዱ ለፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች “በአብዛኛው በሥራ ላይ እየዋሉ ከሚገኙት የሻፊዒይና ሀነፊይ መዝሐቦች የተውጣጡ የሸሪዓ መሠረታዊ ሕግ መድብል (Codified Sharia Laws)” መዘጋጀት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በተቋቋመ የቴክኒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ጋር እንዲሁም ከሕግ ባለሞያዎች የተውጣጣ ኮሚቴ እንዳዘጋጀው የተገለጸው “የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል አስተዳደርን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ የተዘጋጀ” ሠነድ፣፤ ዛሬ እሑድ ኅዳር 22/2017 የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ውይይት ተካሔዶበታል፡፡

በመድረክ ላይ በሠነዱ ላይ በተጨማሪነት ሊካተቱ ይገባቸዋል በተባሉ ጉዳዮች አስተያቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የጠቅላይ ፍርደ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እንዲሁም የእስልምና ሊቃውንት እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው የውይይት መድረክ ለግማሽ ቀን የተከናወነ ነበር፡፡

በመድረኩ ላይ ውይይት የተካሔደበትና “ሚንበር ቲቪ” የተመለከተው ባለ 50 ገጽ የጥናት ሠነድ፤ በአምስት ክፍሎች የተዘጋጀ ነው፡፡ በእነዚህ ክፍሎች የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች “መንግሥታዊ ሃይማኖት በሌላቸው (ሰኩላር) ሀገራት” ያለው ተመክሮ፣ “የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ”፣ “የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የፍትሕ አስተዳደር ችግሮች ትንተና” እንዲሁም “የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ” የተካተተበት ነው፡፡

በተያዘው ወር መጀመሪያ ቀናት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የተረከበው የጥናት ሠነድ፤ በሥራ ላይ ባለው የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አዋጅ ላይ ያልነበሩ ጉዳዮችን ማካተት እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡ በ1992 የጸደቀው የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን አቋም ለማጠናከር የጸደቀው አዋጅ፤ ፍርድ ቤቶቹ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር “የወል ዳኝነት” የሚኖራቸው በውስን ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን አስቀምጧል፡፡ ፍርድ ቤቶቹም የወል ሥልጣን እንጂ የራሳቸው ልዩ ሥልጣን እንደማይኖራቸው ጠቅሷል፡፡

የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንዲመለከቱት በአዋጁ በቀዳሚነት የተቀመጠው “የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናት ሞግዚትነት”ን ነው፡፡ “የወቅፍ፣ የሥጦታ ወይም የኑዛዜ ጉዳዮችን” ደግሞ አዋጁ በሁለተኛነት ዘርዝሯል፡፡

የጥናት ሠነዱ ከጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ “የጋብቻ ውጤት፣ የፍቺ ውጤት፣ ውርስ ማጣራትና ሐብት ክፍፍል” እንዲካተቱ ጠቁሟል፡፡ በዚሁ የወል ዳኝነት ውስጥ “ሸሪዓን መሠረት ያደረገ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የሙአለ ንዋይ ገበያ (ካፒታል ማርኬት)ና ሌሎች የሸሪዓን ሕግ መሠረት አድርገው የተመሠረቱ ስምምነቶችና ግንኙነቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ አለመግባባቶችን” እንዲዳኝ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ሠነድ የፌዴራል የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኝነት መሥፈርትና ሥልጠናን በተመለከተም፤ “የሸሪዓ ሕግ አተረገጓጎምና ወጥነትና ተገማችነት እንዲኖር” በአብዛኛው ሥራ ላይ እየዋሉ ይገኛሉ ብሎ የጠቀሳቸው “ሁለቱ የሸሪዓ ሕግ አተረጓጎም ማለትም ሻፊዒይና ሀኒፊይ መዝሐቦች የተውጣጡ የሸሪዓ መሠረታዊ ሕግ መድብል (Codified Sharia Laws)” መዘጋጀት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡

በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ ቀርቦ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጠበት የጥናት ሠነድ፤ በቀጣይም በሚዘጋጅ ተመሣሣይ መድረክ ግብዐት ለማካተት ተጨማሪ ውይይት እንደሚካሔድበት ተነግሯል፡፡ ለውይይት የቀረበው የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የሚመለከት የጥናት ሠነድ ላይ የተሳተፉት ዳኛ አቶ ሙሐመድ አሕመድ፣ ዳኛ ሸይኽ አሕመድ አደም፣ ዶክተር ሸይኽ ሙሐመድ ሐሚዲን፣ አቶ ሻፊ ዘለቀ እና አቶ ዓብዱልሐኪም ጀማል መሆናቸውን በሠነዱ ላይ ሠፍሮ ይገኛል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular