በፍልስጤም ጉዳይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ መዝገብ ለማስከፈት ሁሉም መስፈርቶች መሟላታቸው ግልጽ ሆኗል፡፡ ይህ የእኔ አስተያየት አይደለም፤ እውነታው እንደዚያ ነው፡፡ መንግሥታትም ቢሆን ከየትኛው ጎራ እንደተሰለፉ መለየት አለባቸው፡፡ ሁለት ጎራ ነው ያለው፤ ለሰብዓዊ መብቶች አጋርነታቸውን ማሳየት አልያም ከዘር ፍጅት ጋር መቆም፡፡
የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤም የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስቆም አንዳችም ነገር ሳያደርጉ ስለ ዓለም አቀፍ ሕግ እና ስለ ሰብዓዊ መብቶች መከበር የመናገር ድፍረት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ምንም ነገር ካላደረገም መጨረሻው ይሆናል፡፡ እኛ በኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ለማውጣት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ሰብስበናል፡፡
ይህ የተናገሩት ፈረንሳዊው የሕግ ባለሞያ ጋይልስ ዲቬርስ ናቸው፡፡ ዴቨርስ በርካታ ዓመታትን ያሳለፉት ለፍልስጤማዊያን በፍርድ ቤት ሲሟገቱ ነው፡፡ የእስራኤል ወታደሮች በሚሰነዝሩት ርሕራሄ በጎደለው የቦንብ ጥቃት፤ ጉዳት የደረሰባቸውን በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ፍልስጤማዊያንን ዶሴ ሰብስበው ችሎት ፊት ሲሟገቱ ኖረዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን ንግግር በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ቀርበው ያደረጉት ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ነበር፡፡ የሕግ ባለሞያው ይህን የተናገሩት ለዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት እርሳቸው በመሪነት ቆመው ከሌሎች ሦስት ጠበቆች ጋር የእስራኤልን ወንጀል ለማጋለጥ ለሙግት በተዘጋጁበት ወቅት ነበር፡፡ ጋይልስ ዲቬርስ ለፍርድ ቤቱ ዶሴ ያሰባሰቡት የእስራኤል ባለሥልጣናት የፈጸሙትና እየፈጸሙ የሚገኙት የዘር ፍጅት መሆኑን ተከራክረው ለመርታት ነበር፡፡
በወቅቱ የ67 ዓመት እድሜ የነበራቸው ፈረንሳዊው የሕግ ባለሞያ፤ በችሎት ፊት ሙግታቸው ቢያሸንፉ የመጨረሻ ግብ አድርገው ያስቀመጡት፤ ያለፉትን ዓመታት በፍልስጤማዊያን ላይ ሕጻን – አዋቂ ሳይመርጥ እጅግ አስከፊ ወንጀሎችን ሲፈጽም የቆየውን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር በችሎት ፊት ማቆም ነው፡፡ ብርቱው የሕግ ባለሞያ ዲቬርስ ለዚህ መንገዳቸው ከጎናቸው በርካቶችን ማሰለፍ ስለነበረባቸው ይህንኑ አደረጉ፡፡ 800 አባላት ያሉትን ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሞያዎች ኔትወርክ መመሥረት ቻሉ፡፡

ጋይልስ ዲቬርስ ከባልደረቦቻቸው ጋር ቀን ከሌት የለፉበት ጉዳይ ያለፉትን ወራት ስለፍትሕ በሚቆሙ ሰብዓዊ ፍጡራን ሲጠበቅ የነበረ ነው፡፡ እንደመታደል ሆኖ እነ ጋይልስ ዲቬርስ ልፋታቸው አንዲሁ መና አልቀረም፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ኅዳር 12/2017 ከሰዓት ላይ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዜናውን ይፋ አደረገ፡፡ ዜናው በቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ መቆረጡን የሚገልጽ ነበር፡፡ መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ሔግ ያደረገው ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት፤ ማዘዣውን ሲያወጣ ከቤንያሚን ኔታንያሁ በተጨማሪ በመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ቆርጧል። ኔታኒያሁና የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ላይ የወጣው ማዘዣ ጋይልስ ዲቬርስ ሲጠይቁት እንደነበረው በጋዛ ፈጽመውታል በተባለው “የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል” ምክንያት የተቆረጠ ነው።
ጉዳዩን የያዙት ዳኞች፤ ሁለቱ ግለሰቦች ቢያንስ ከባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ቀናት ወዲህ ባሉት አስራ አራት ወራት ገደማ፤ “በጋዛ ለሚገኙ ንጹሐን ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ማለትም ምግብን፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እና መድኃኒቶችን እንዲሁም የሕክምና አቅርቦቶችን ነዳጅ እና ኤሌክትሪክ ጭምር እንዳያገኙ ሆን ብለው መከልከላቸውን ለማመን የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች እንዳሉ ተገንዝበናል” በማለት የእስር ማዘዣውን ያስፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
ይህ ቀን የፈረንሳዊው የሕግ ባለሞያ ጋይልስ ዲቬርስ ሕልም በእውን የተገለጠበት ነበር፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ ግን ዲቬርስ ዜናውን ሲሰሙ ዕድሜ ሕመም ደርቦባቸው አልጋ ላይ ነበሩ፡፡ በርግጥ ባልደረቦቻቸው እንዳሉት ከሆነ ያለፉትን ጊዜያት ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው ከሚችል ሕመም ጋር እየተጋፈጡ ነበር የፍርድ ቤቱን ጉዳይ የሚከታተሉት፡፡ ከሕግ ባለሞያ ከመሆናቸው አስቀድሞ ሕክምና ያጠኑት ሰው፤ ጤናቸው ተቃውሶ ፋታ አልሰጥ ቢላቸውም በፍልስጤማዊያን ጉዳይ የሚተኙ አልሆኑም ነበር፡፡
በቅርብ ጓደኛቸውና በሌላኛው ፈረንሳዊ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ ዓብዱልመጂድ ሜራሪ ‹‹ለሰብዓዊነት እና ለመርህ የታመኑ›› ተብለው የሚገለጹት ጋይልስ ዲቬርስ፤ ከዚህ ቀደም ለሕይወታቸው አስጊ የሚባል የቀዶ ጥገና ለማድረግ ሆስፒታል አልጋ ላይ ሆነው እንኳን በመጨረሻው ሰዓት ያነሱ የነበረው የፍልስጤማዊንንን ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አጋጣሚ በፍልስጤማዊያን ንጹሐን ጉዳይ እንባ አውጥተው ሲያለቅሱ መመልከቱንም ዓብደልመጂድ ያስታውሳል፡፡

እኚህ የተከበሩ የሕግ ባለሞያ ባለፈው ሳምንት የኔታንያሁ የእስር ማዘዣ ዜና ይፋ ሲደረግ፤ አልጋ ላይ ሆነው ከሕመማቸው ጋር እየታገሉ የነበረ ቢሆንም፤ ሰውዬው ላይ እስር ማዘዣ መውጣቱን ሰምተው ተደስተዋል፡፡ ለዓመታት የለፉለት ጉዳይ ቢያንስ ግማሽ መንገድ ተጉዟል፡፡ ከፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ የወጡት ጋይልስ ዲቬርስ፤ ሲጠብቁት የቆዩት ጉዳይ መሳካቱን ሲያውቁ ግን “በምድር ቆይታ ከዚህ በላይ ማሳካት የሚሹት አልነበረም ወይ?” በሚያስብል ሁኔታ ብዙ አልቆዩም፡፡ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ከምድር ሕይወት ሕይወት የመሸኘታቸው አሳዛኝ ዜና በቤተሰቦቻቸው በኩል ይፋ ተደረገ፡፡ ለ ሞንድ የተሰኘው የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንዳስነበበው ከሆነ፤ ከመሔዳቸው በፊት ልጃቸውን ጠርተው ‹‹በል ይበቃል፤ አሁን በሰላም ልሒድ›› ብለውታል፡፡
ከሽኝታቸው በኋላ ለሚድል ኢስት ሞኒተር የተናገረው የቅርብ ጓደኛቸው ዓብዱልመጂድ ሜራሪ፤ የኔታንያሁ የእስር ማዘዣ ለጋይልስ ዲቬርስ “የ15 ዓመታት ልፋት የተበረከተ ሥጦታ ነው” ብሏል፡፡ የእነ ኔታንያሁ ጉዳይ በእስር ማዘዣ መውጣት በቃ የሚባል አለመሆኑንም በዚሁ ያስታወሰው ሜራሪ፤ እውነተኛውና አስቸጋሪው ሥራ ከዚህ በኋላ ያለው መሆኑን በመጠቆም ለዚህ ደግሞ ስለፍልስጤማዊያን ሲለፉ የቆዩትን የጋይልስ ዲቬርስን ብርታት መዋስ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ተናግሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












