Homeዜናና ወቅታዊዜናበአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ስር የሚተዳደረው የዐይነ ሥውራን ት/ቤት የጣለው የሰላት ክልከላ...

በአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ስር የሚተዳደረው የዐይነ ሥውራን ት/ቤት የጣለው የሰላት ክልከላ መነሳቱን ተማሪዎች ተናገሩ

በአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ስር የሚተዳደረው በከተማዋ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው “ክብርት ሸይኻ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት”፤ በግቢው ውስጥ ሰላት እንዳይሰገድ የጣለው ክልከላ መነሳቱን ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ የትምሕርት ቤቱ ርእሰ መምሕርት ለተማሪች ሰላት እንዲሰግዱ መፈቀዱን ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡

የ“ክብርት ሸይኻ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት”፤ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሰላት እንዳይሰገዱ የጣለው ክልከላ ማንሳቱን የገለጸው ረቡዕ ኅዳር 18/2017 መሆኑን ተማሪዎች ለ“ሚንበር ቲቪ” ገልጸዋል፡፡ ከተማሪዎች እንደተሰማው ከሆነ ክልከላው መነሳቱን የገለጹት የትምሕርት ቤቱ ርእሰ መምሕርት ወይዘሮ ዓለም ከበደ ናቸው፡፡

የትምሕርት ቤቱ የሰላት ክልከላ መነሳት ዜና የመጣው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተማሪዎች የሰላት ክልከላ ጉዳይ በኃላፊዎቹ በኩል ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ውይይት ማካሔዱ ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡ ተማሪዎች እንደገለጹት፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት ሰላት እንዳይሰግዱ የተከለከሉ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር መፍትሔ እንዲሰጣቸው ውይይት አድርገው የነበረ ቢሆንም አዎንታዊ ምላሽ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ የትምህርት ቤቱ አስተዳደሩ በግቢ ውስጥ ሰላት መስገድ እንደማይፈቅድ አስታውቋል፡፡

አስተዳደሩ በተማሪዎች ላይ የጣለውን ክልከላ በተመለከተ በወቅቱ ከሚንበር ቲቪ ጥያቄ የቀረበላቸው ርእሰ መምህርቷ ወይዘሮ ዓለም ከበደ ምንም ዐይነት ክልከላ አልጣልንም ሲሉ የተማሪዎቹን ቅሬታ ቢያስተባብሉም ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኞ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር፡፡ ነገር ግን እኚሁ ርእሰ መምህርት ረቡዕ ኅዳር 18/2017 ተማሪዎቹን ከዚህ በኋላ በማደሪያ ክፍላቸው መስገድ እንዲችሉ መፈቀዱን መናገራቸውን ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በግቢው ውስጥ የመስገጃ ሥፍራ ማዘጋጀቱም ተነግሯል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ውይይት መካሄዱን የገለጸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ከውይይቱ በኋላ ማጣራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጾ ነበር፡፡ በዛሬው እለት እንደተሰማው ከሆነ የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በትምህርት ቤቱ በመገኘት ማጣራት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ሆኖም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ጉብኝቱን ስለማድረጋቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተመረቀው የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምሕርት ቤቱ፤ ተማሪዎችን መቀበል የጀመረው በጳጉሜን ወር 2016 ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ወር አጋማሽ በተመሣሣይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ቢያንስ አምስት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች ኒቃብ ለብሳችሁ በትምሕርት ገበታ ላይ መገኘት አትችሉም እንደተባሉ በመግለጽ ቅሬታቸው አቅርበው ከከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ምክር ቤቱ ጥቅምት 21/2017 ከአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ፣ ከሠላም እና ፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተገናኘ “ምክረ ሐሳብ” ለማቅረብ “ከስምምነት ላይ መደረሱን” አስታውቆ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ እስካሁን ድረስ ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ስለመኖሩ ያወጣው መረጃ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular