Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችሐማስ የዶሐ ጽሕፈት ቤቱን እየለቀቀ ይሆን?

ሐማስ የዶሐ ጽሕፈት ቤቱን እየለቀቀ ይሆን?

የፍልስጤሙ ሐማስ በዶሐ የሚጠቀምትን ጽሕፈት ቤት ሊቀቅ ነው የሚሉ መረጃዎች መውጣት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ለመረጃው መሠራጨት መነሻ የሆነው ቡድኑን ከእስራኤል ጋር ከሚያሸማግሉት መካከል የሆነችው የባሕረ ሰላጤዋ ሀገር “ተደራዳሪዎቹ ለሽምግልና ቁርጠኛ አቋም እያሳዩ አይደለም” በሚል ከሒደቱ መውጣቷን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኩል ይፋ ማድረጓ ነው፡፡

መረጃውን የተቀባበሉት በዋነኝነት እስራኤል መገናኛ ብዙኃን ከምዕራባዊያን አጋሮቻቸው ጋር በአንድነት ‘ሐማስ በኳታር የመቆየቱ ጉዳይ ያበቃለት ሆኗል’ የሚል ይዘት ያላቸውን ዘገባዎች ሲያጋሩ ቆይተዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ለዜናቸው ዋቢ ሲያደርጉ የቆዩት ሥማቸው የማይጠቀሱ “የዲፕሎማቲክ እና ባለሥልጣናት” ምንጮችን ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ዘገባ ለሠሩ መገናኛ ብዙኃን መረጃው “ትክክለኛ ነው” ብሎ ማረጋገጫ የሰጠ ሥሙ እና ሥልጣኑ በግልጽ የተጠቀሰ የሐማስም ሆነ የኳታር ባለሥልጣን እስካሁን ድረስ አልታየም፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ማክሰኞ በቃል አቀባዩ በኩል የተለመደ ጋዜጣዊ መግለጫውን በሚሰጥበት ወቅት የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ዶክተር መጂድ ቢን ሙሐመድ አል አንሳሪ፤ ጉዳዩን አንስተው የሰጡት ማብራሪያ የመገናኛ ብዙኃኑን ቀደመ ዜና ይበልጥ እያራገበው ይገኛል፡፡ አል አንሳሪ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ሀገራቸው ድርድሩን በማቆም ላይ የቀየረችው አቋም ባይኖርም የሐማስ የዶሐ ጽሕፈት ቤት አለመዘጋቱን ግን አረጋግጠዋል፡፡

‘ለድርድር ሒደት የተከፈተ ነው’ ያሉትን ጽሕፈት ቤት ‘ቢዘጋ የምትሰሙት በሌላ መንገድ ሳይሆን ከእኛ ከራሳችን በቀጥታ ነው’ ሲሉም የመገናኛ ብዙኃኑን መረጃ ውድቅ የሚያደርግ ንግግር አድርገዋል፡፡ ቃል አቀባዩ አያይዘው የጠቀሱት ጉዳይ የሐማስ ከፍተኛ ኃላፊዎች በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ሥፍራ ነው፡፡ እንደ ዶክተር መጂድ ቢን ሙሐመድ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት የሐማስ ከፍተኛ ኃላፊዎች በዶሐ ውስጥ እንደማይገኙ በመግለጽ፤ “እንደምታውቁት [የሐማስ መሪዎች] በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

ሐማስ ባለፈው ሰሞን የኳታር ጽሕፈት ቤቱን ሊዘጋ ነው የሚሉ የመገናኛ ብዙኃንን ዘገባዎችን ተከትሎ ቀጣይ መዳረሻው ወዴት ሊሆን ይችላል በሚል ከተጠቀሱት መካከል የረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ሀገር ቱርክ በቀዳሚነት ተጠቅሳለች፡፡ ነገር ግን ቱርኪዬ ቱዴይ የተሰኘ የሀገሪቱ የዜና ወኪል፤ የቱርክ ባለስልጣናት ሐማስ በሀገሪቱ ቋሚ ቢሮ ለመክፈት ምንም ዕቅድ እንደሌለው በመግለጽ ዘገባዎቹን ውድቅ ማድረጋቸውን አስነብቧል፡፡

ሐማስ በዶሐ የሚገኘውን ጽሕፈት ቤቱን የከፈተው እ.አ.አ በ201 ነበር፡፡ የኳታር ባለሥልጣናት እንደሚሉት ጽሕፈት ቤቱ የተከፈተው በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤ “ከሐማስ ጋር የግንኑኘት መስመር እንዲኖር በመጠየቃቸው ነው”፡፡ የፍልስጤሙ ቡድን እስካሁን ድረስ ጽሕፈት ቤቱን በተመለከተ ስለሚወጡት መረጃዎች አንድም ይፋዊ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular