Homeዜናና ወቅታዊዜናከኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በኋላ በውጭ ክትትል የሚያደርጉ ታካሚዎች ከጳውሎስ ሆስፒታል መድኃኒት...

ከኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በኋላ በውጭ ክትትል የሚያደርጉ ታካሚዎች ከጳውሎስ ሆስፒታል መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

ከኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በኋላ ከሆስፒታሉ ውጭ ክትትል የሚያደርጉ ታካሚዎች በሀገሪቱ በብቸኝነት ሕክምናውን ከሚሰጠው ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም ሲሉ አቀረቡ። የሆስፒታሉ ኃላፊ በበኩላቸው የተደረገ ክልከላ የለም በማለት ቅሬታውን ውድቅ አድርገዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም ያሉ ቅሬታ አቅራቢ ለ“ሚንበር ቲቪ” ቅሬታቸውን አቅርበል። የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከማድረጋቸው በፊት በሆስፒታሉ የዲያሌሲስ አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸውን የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዋ፣ ሕክምናና ክትትሉን ከሆስፒታሉ ውጪ በማድረግ “ለዕድሜ ልክ የሚወሰድ ነው” ያሉትን መድኃኒት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በግዥ ያገኙ እንደነበር ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የአሠራር ለውጥ በማድረጉ ሳቢያ ግን መድኃኒቱን ማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል። ታካሚዋ ሆስፒታሉ የሚወስዷቸውን “አራት መድኃኒቶች” መስጠት በማቆሙ በግል ተቋማት በጳውሎስ ሆስፒታል ከሚገዙበት ሁለት ሺሕ ብር ገደማ በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ለመክፈል ተገድጃለሁ ብለዋል። ይህም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ታካሚዎችን የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል። ይህን ቅሬታቸውን ከሌሎች ታካሚዎች ጋር በመሆን ለሆስፒታሉ ኃላፊዎች ቢያቀርቡም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘንም ብለዋል።

በታካሚዎች የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ “ሚንበር ቲቪ” ያነጋገራቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ውለታው ጫኔ፣ ሆስፒታሉ ከንቅለ ተከላ በኋላ ክትትል ለሚያደርጉ መድኃኒት መስጠት አቋርጧል መባሉን ውድቅ አድርገውታል። በአንጻሩ አዲሱ አሠራር የሚጠይቀው ታካሚዎች በሆስፒታሉ ካርድ አውጥተው እንዲመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ታካሚው ክትትሉን ሌላ ቦታ ማድረጉንም ቁጥጥርም ሆነ ክልከላ ሊደረግበት የሚቻል ነገር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ውለታው ጫኔ

“መድኃኒቱን ለማግኘት ቢያንስ እኛ ጋር [በኛ ዳታ ቤዝ] ሊመዘገቡ ይገባል” ያሉት ዶክተር ውለታው፣ “መድኃኒት ስንጠይቅ ባሉን ታካሚዎች ልክ ስለምንጠይቅ፣ ሌላ ቦታ ይህን ያህል ታካሚ ሊኖር ይችላል ብለን መገመት አንችልም” ሲሉ ሒደቱን አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመድኃኒቱን ዋጋ ውድ መሆን በማንሳት፣ “ከታካሚው ቁጥር በላይ ካዘዝን ጊዜው ያልፍበታል። መድኃኒቱ ደግሞ በጣም ውድ ስለሆነ ኪሳራው ከፍተኛ ነው” ብለዋል። ታካሚዎች ካርድ በማውጣት “የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሞያ ተመልክቷቸው መድኃኒቱ እንዲወሰድ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ” ማግኘት እንደሚችሉም ገልፀዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አስር ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አድርገው የሕክምና ክትትል ከሚያደርጉት በተጨማሪ በርካቶች አገልግሎቱን ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular