የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ያቀረበውን ጋዛ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቀውን የፀጥታው ምክር ቤት ረቂቅ ውሳኔ ሐሳብ፤ አሜሪካ ውድቅ ያደረገችው ለ49ኛ ጊዜ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁን ያቀረቡት 10 የምክር ቤት አባላት በሙሉ ውሳኔውን ቢደግፉትም አሜሪካ ግን ውድቅ አድርጋዋለች፡፡
ከውሳኔው በኋላ የተናገሩት የማልታ ተወካይ ቫኔሳ ፍራዚየር፤ “ይህ ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነትን የማስከበር ኃላፊነቱን በድጋሚ ባለመወጣቱ በጣም ያሳዝናል” ያሉ ሲሆን፣ የአሜሪካን ድርጊትም ነቀፌታ ሰንዝረውታል፡፡
የውሳኔ ሐሳቡን ካቀረቡት መካከል አልጄሪያ፣ ኢኳዶር፣ ጉያና፣ ማልታ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ስሎቬኒያ እና ስዊዘርላንድ ይገኙበታል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በጋዛ “አስቸኳይ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ቋሚ” የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው፡፡ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ፍልስጤማውያን እንዳይራቡ መከላከል እንዳለባቸው የሚል አንቀጽ ሠፍሮበታል፡፡
በጋዛ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ ቀውስ በማጉላት “በጋዛ ያሉ ንጹሐን ለሕልውናቸው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችንና ሰብአዊ ድጋፎችን በአስቸኳይ እንዲያገኙ”ም ጠይቋል። “የፍልስጤማውያንን ረሐብ ለማባባስ የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት” ውድቅ በማድረግም “የሰብዓዊ ርዳታ በመላው ጋዛ እንዲቀርብ “በአስቸኳይ፣ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲሁም ያለገደብ እንዲገባ” ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ90 ቀናት ውስጥ ስለ አዋጁ አፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብ ለጋዛ የሚያስፈልገውን ሁሉን አቀፍ ግምገማ እንዲያቀርብ ጠይቋል። ሆኖም የአሜሪካ ተወካይ የሀገሪቱን ድምጽ በድምጽ የመሻር ርምጃ እነዚህ ውሳኔዎች እንዳይተገበሩ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አንድ የውሳኔ ሐሳብ እንዲፀድቅ በድጋፍ ቢያንስ ዘጠኝ ድምጽ ማግኘት ያለበት ሲሆን፣ ከምክር ቤቱ አምስቱ ቋሚ አባላት መካከል የተቃውሞ ድምጽ ማቅረብ አይኖርባቸውም፡፡
በምክር ቤቱ ሁለተኛው የአሜሪካው ተወካይ አምባሳደር ሮበርት ዉድ በሰጡት መግለጫ፤ ሀገሪቱ በጋዛ ውስጥ በሐማስ ተይዘዋል ያሏቸው ምርኮኞች ጉዳይ ከተኩስ አቁም ድርድሩ ጋር አብሮ እንዲካከት ትፈልጋለች፡፡ አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውሳኔን ከመሻሯ በፊት አስተያየት የሰጡት የጉያና ተወካይ ካሮሊን ሮድሪጌስ ቢርኬት፤ ለውሳኔ የቀረበው ሐሳብ ሁሉም ምክር ቤት አባላት ለበርካታ ሳምንታት ያደረጉት ምክክር ውጤት መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
አሜሪካ ያሳለፈችው ውሳኔ በጋዛ ጉዳይ ለአንድ ዓመት ያህል ለእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ሽፋን መስጠቷን እንደቀጠለች አመልካች መሆኑን በጉዳዩ ላይ የጻፉ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ ለእስራኤል በየዓመቱ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ ርዳታ ከመስጠቷ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የእስራኤሉ ትልቋ አጋር መሆኗን ባለሥልጣኖቿ በአደባባይ ይናገራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












