Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ

ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ

መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ሔግ ያደረገው ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና መከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል። ማዘዣው የወጣው ከሪም ኻን የሚመሩት የዳኞች ቡድን ጥያቄውን ካቀረበ ከስድስት ወራት በኋላ ነው።

ዛሬ ሐሙስ ይፋ የተደረገው የእስር ማዘዣ በወንጀለኛ ፍርድ ቤቱ ታሪክ የምዕራባዊያን ሀገር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ተግባራዊ የተደረገ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል። ኔታኒያሁና የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ላይ የወጣው ማዘዣ በጋዛ ፈጽመውታል በተባለው የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ምክንያት የተቆረጠ ነው።

ምክር ቤቱ የእስር ትዕዛዞቹ “ምስጢራዊ” ተብለው የተለዩ ቢሆንም “በማዘዣው ላይ ከተጠቀሰው ጋር የሚመሳሰል ድርጊት እየተካሄደ ያለ ይመስላል” በማለት ይፋ እንዲደረጉ ውሳኔ ማሳለፉን ባወጣው መግለጫ ላይ ምክንያቱን አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪም የወንጀል ድርጊቱ ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው ስለ ማዘዣው ዝርዝር እንዲያውቁ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም ጠቅሷል።

እ.አ.አ በ2002 በተቋቋመው ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት፤ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ለማውጣት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ከተነገረ ወራት ተቆጥሯል፡፡ የወንጀለኛ ፍርድ ቤቱ በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሥልጣን ያለው ቢሆንም የማስፈፀም አቅሙ ላይ ጥርጣሬ ይነሳበታል።

በነቃፊዎቹ በተለይ አፍሪካዊያን ላይ ብቻ ይበረታል ተብሎ ሐሜታ የሚቀርበበት ዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት፤ የመጀመሪያው ሥምምነት የተደረገው በሮም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሐምሌ 1998 ነበር፡፡ ድርጅቱ በ2002 በይፋ ሥራውን የጀመረው ከዚህ ስምምነት በኋላ ከ60 በላይ ሀገራት ስምምነቱን ካጸደቁለት በኋላ ነው፡፡ የሮሙ የመመሥረቻ ስምምነት በእነዚህ ሀገራት ተፈርሞ ቢጸድቅም አሁንም ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራቅ፣ ሰሜን ኮርያ እና ሳዑዲ ዐረቢያ አላጸደቁትም፡፡

ፍርድ ቤቱ የሚያወጣቸው የእስር ማዘዣዎች ሥምምነቱን ባፀደቁ ከ120 በላይ ሀገራት ተፈፃሚ ሊሆን እንደሚገባ አሥፍሯል። በዚህም ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ በመውጣቱ ሁለቱ ሰዎች የሀገራቱን መሬት የሚረግጡ ከሆነ ለፍርድ ቤቱ የማስረከብ ግዴታ የአስተናጋጅ ሀገራት መሪዎች ላይ የሚወድቅ ይሆናል ተብሏል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተለያዩ አስተያቶችን እያስተናገደ ይገኛል። ከውሳኔው በኋላ ፍርድ ቤቱ የሚገኝባት ኔዘርላንድስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለማዘዣው ተፈጻሚነት እሠራለሁ ብላለች። በፍርድ ቤቱ የፍልስጤም ተጎጂዎችን የሚወክሉት ጠበቃ ትሪስቲኖ ማሪኒዬሎ የፍርድ ማዘዣውን መውጣት “ታሪካዊ ውሳኔ” ያሉት ሲሆን፣ ከአሜሪካ መንግሥት “ጫናና ማስፈራሪያ” ደርሶበታል ያሉት ፍርድ ቤት የወሰደው ርምጃ ህጋዊነቱን ለማጽናትና ለተዓማኒነቱ ወሳኝ ነው” ሲሉ ለሚድል ኢስት ዐይ ገልፀዋል።

ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር በተጨማሪ በሐማስ መሪ ሙሐመድ ዳኢፍ ላይ የእስር ማዘዣ የቆረጠው ፍርድ ቤት እስካሁን ድረስ በተለይ መሠረታቸውን አፍሪካ ያደረጉ ከሐምሳ በላይ ግለሰቦችን ክስ ሰምቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል አስር ሰዎች የመጨረሻ ፍርድ ሲሰጣቸው፤ አራቱ ነጻ ተብለዋል፡፡
(ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular