- በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ምላሽ መስጠት አልቻሉም
- ክልከላውን የጣለው ትምሕርት ቤት ርእሰ መምሕርት ““ምንም ክልከላ አላደርግንም” ከማለት ውጭ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል
በአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ስር የሚተዳደረው በከተማዋ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው “ክብርት ሸይኻ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት”፤ ሰላት እንዳይሰገድ መከልከሉን ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡ በትምሕርት ቤቱ ሙስሊም ተማሪዎች ሰላት እንዳይሰግዱ ክልከላ ከመጣሉ በተጨማሪ ሴት ተማሪዎች ኒቃብ ለብሰው እንዳይገቡ በመደረጋቸው ወደመጡበት እንዲመለሱ መገደዳቸው ታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተመረቀው የአዳሪ ትምሕርት ቤቱ፤ ተማሪዎችን መቀበል የጀመረው በጳጉሜን ወር 2016 መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ወደ ትምሕርት ቤቱ ገብተው ከነበሩ ከተማሪዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል በአሁኑ ሰዓት በተጣለው ክልከላ ምክንያት ትምሕርት ለማቋረጥ መገደዱን የተናገረው ጀማል ኢብራሂም፤ የሰላት ክልከላውም ሆነ ሌሎች እስላማዊ ግዴታዎች የተጣሉት ገና “ለትምሕርት በገቡበት ወቅት” ላይ እንደነበር ገልጿል፡፡

ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ የገለጸው በዐይነ ስውራን ላይ የሚሠራው የዓብደላ ኢብን መኽቱም የቁርኣን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኸድር ሙሐመድ፤ በአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ስር የሚተዳደረው ትምሕርት ቤት ተማሪዎች ቅሬታ ደርሶት እንደነበር በመግለጽ፤ ቅሬታውን በመያዝ ለሚመለከተው ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለሁለት ጊዜ ደብዳቤ በመጻፍ መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ሰላት ከመከልከላቸው በተጨማሪ “በልምድ ልውውጥ” ሰበብ “ስብከት እንደሚቀርብላቸው እንዲሁም መዝሙር እንዲዘምሩ እንደሚደረጉ” የጠቆሙት አቶ ጀማል፤ መፍትሔ እንዲሰጥበት ለቀረበው ቅሬታ ከከተማው ምክር ቤት ምላሽ ባለማግኘቱ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተመሳሳይ ደብዳቤ መጻፋቸውን አስረድተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ “ሚንበር ቲቪ” ማኅበሩ ደብዳቤ ከጻፈለት ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ የተሳካ ቢሆንም ኃላፊዎቹ ማብራሪያ መስጠት ባለመቻላቸው ማካተት አልተቻለም፡፡
ቅሬታውን በተመለከተ በተማሪዎች የሰላት ክልከላ ጥሏል የተባለውን የ“ክብርት ሸይኻ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ሥውራን አዳሪ ትምሕርት ቤት” ርእሰ መምሕርት ወይዘሮ ዓለም ከበደን በተመሣሣይ ማግኘት የተቻለ ቢሆንም በተማሪዎች ላይ “ምንም ክልከላ አላደርግንም” የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጭ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ወር አጋማሽ በተመሣሣይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ቢያንስ አምስት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች ኒቃብ ለብሳችሁ በትምሕርት ገበታ ላይ መገኘት አትችሉም እንደተባሉ በመግለጽ ቅሬታቸው አቅርበው ከከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ምክር ቤቱ ጥቅምት 21/2017 ከአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ፣ ከሠላም እና ፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተገናኘ “ምክረ ሐሳብ” ለማቅረብ “ከስምምነት ላይ መደረሱን” አስታውቆ ነበር፡፡
ምክር ቤቱ የሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ ከፌዴራል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በአንድነት የሚዘጋጅ መሆኑንም በወቅቱ ገልጿል፡፡ ይህን ከገለጸ አንድ ወር ገደማ የተቆጠረ ቢሆንም ስለ ምክረ ሐሳቡ ዝግጅት እስካሁን ድረስ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡
አሁን በዐይነ ሥውራን ተማሪዎች ላይ የሰላት እና እስላማዊ አለባበስ ክልከላ መጣሉ በተነገረው በ“ክብርት ሸይኻ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት” ትምሕርታቸውን የሚከታተሉ ሙስሊም ተማሪዎች ብዛት ከ100 በላይ እንደሚገመት ከተማሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












