Homeዜናና ወቅታዊዜናጠቅላይ ምክር ቤቱ በቀጣይ ለሚያደርገው ምርጫ የከተማ አስተዳደሩን “ድጋፍና እገዛ”  መጠየቁን ገለጸ

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቀጣይ ለሚያደርገው ምርጫ የከተማ አስተዳደሩን “ድጋፍና እገዛ”  መጠየቁን ገለጸ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ለሚያካሔደው ምርጫ የአዲስ አበባ አስተዳደርን “ድጋፍና እገዛ” መጠየቁን ገልጿል።

ምክር ቤቱ ይህን የገለፀው በፕሬዝዳንቱ የተመራ የከፍተኛ አመራር ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ሰኞ ኅዳር 16/2017 “የሙስሊሙን ማኅበረሰብ የቀረቡ፣ ያልተፈቱ እና አዲስ ጥያቄዎችን” አስመልክቶ ውይይት ማድረጉን ባሳወቀበት መግለጫ ነው። እንደ ምክር ቤቱ ከሆነ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች ስድስት ናቸው።

መግለጫው ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መካከል የሦስት ዓመት ጊዜያቸውን የሚያጠናቅቁ አመራሮችን ለመተካት ምርጫ ለማካሔድ በእቅድ ተይዟል ያለው የምርጫ ጉዳይ ይገኝበታል። ምክር ቤቱ ለዚህ ምርጫ የከተማ አስተዳደሩን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ይህ የምክር ቤቱ መግለጫ፣ ለከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና እገዛ እንዲያደግለት መጠየቁን ከመጥቀስ ባሻገር በድጋፍ እና እገዛ የተጠየቀው ጉዳይ እንዲሁም የተሰጠው ምላሽ ምን እንደሆነ የተጠቀሰበት አይደለም።

ከከንቲባዋ ጋር የነበረውን ቆይታ በተመለከተ የጻፉት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፣ ውይይቱን “ፍሬያማ” ነበር ቢሉም ዝርዝር ጉዳዮችን አልገለጹም።

በውይይቱ ላይ እርሳቸውን ጨምሮ የየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት ሸይኽ ዓብዱልከሪም በድረዲን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተገኝተዋል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ምርጫ አካሔዳለሁ ያለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን ከወጡ
ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ አስቆጥረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው የሥልጣን ጊዜ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ባለፈው ዓመት አጋማሽ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና ከክልሎች ከመጡ አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ላይ መንግሥት ለምርጫው እገዛ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት ላይ ስለ ምርጫ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ጊዜው ሲደርስ “ከሕዝብ ነው የተረከብነው፤ ለሕዝብ እናስረክባለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አክለውም በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከመጅሊስ ላይ “መቶ በመቶ እጁን አንስቶ” በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይ ምርጫ መንግሥት እንዲያግዛቸው ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ይህን ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ “ጣልቃ ገብ እንድትሆኑ” አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ እንደ መንግሥት መጪው ምርጫ ላይ አግዙን የምንለው “አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ እንድታመቻቹልን ነው” በማለት ከመንግሥት የሚፈልጉትን እገዛ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር እንዳሳወቀው ለምርጫ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ መመሪያ ያዘጋጃል። ፕሬዝዳንቱ ነሐሴ 27/2016 ለዑለማ ምክር ቤት እና ለአማካሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፈው የነበረ ቢሆንም የተጠየቀው ሰነድ እስካሁን ድረስ ስለመቅረቡ ምክር ቤቱ የገለጸው ነገር የለም። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular