Homeዜናና ወቅታዊዜናየሚያንማር ፕሬዝዳንት በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ የሚጠይቅ...

የሚያንማር ፕሬዝዳንት በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ የሚጠይቅ ማመልከቻ ቀረበ

ዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የሚያንማር ፕሬዝዳንት ሚን አውንግ ሃላይንግ፤ በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥበት የሚጠይቅ ማመልከቻ አቅርቧል፡፡ የፍርድ ቤቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ ከሪም ኻን ይህንኑ ይፋ ያደረጉት በዛሬው እለት ነው፡፡

በፕሬዝዳንቱ ላይ የቀረበው የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ የሚጠይቀው ማመልከቻ በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ በሚገኝ ባለሥልጣን ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዋና ዐቃቤ ሕጉ የመጀመሪያውን ማመልከቻ በፕሬዝዳንቱ ላይ ቢያቀርቡም በቀጣይ በሌሎች የወንጀሉ ተባባሪ ባለሥልጣናት ላይ የማዘዣ ጥያቄው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሚያንማር ፕሬዝዳንት ሚን አውንግ ሃላይንግ

ከሪም ኻን ስለ ጉዳዩ በተናገሩት ወቅት፤ ‘ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ይህን ማድረጋችን በሮሂንጋ የሚገኙ ሰዎች ልክ በሌሎች ዓለማት እንደሚገኙ የሕግ ከለላ እንደሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ እንዳልተዘነጉ ማሳየት እንፈልጋለን’ ብለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ሦስት ዳኞችን የያዘ ቡድን ማስረጃዎች ላይ ምርመራ በማድረግ የእስር ማዘዣውን እንዲቆረጥ የማስፈጸም ተልዕኮ ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡

እ.አ.አ በ2017 በርካታ ቁጥር ያላቸው የሮሂንጋ ሙስሊሞች በሚያናማር መንግሥት የተከፈተባቸውን የዘር ማጥፋት በመሸሽ ወደ ጎረቤት ባንግላዴሽ ገብተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከሆነ፤ የሚያንማር የፀጥታ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ ራኺን ግዛት የቀሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ቀጥለውበታል፡፡

በሮሂንጋ የሚያንማር የፀጥታ ኃይሎች ከሚያደርሱባቸው ስቃይ በመሸሽ ወደ ጎረቤት ባልግላዴሽ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ700 ሺሕ በላይ እንደሚገመት ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዐቃቤ ሕጉ ከሪም ኻን በዛሬው መግለጫቸው ጽሕፈት ቤታቸው እነዚህ ወንጀሎች የተፈፀሙት ከነሐሴ 25/2017 እስከ ታኅሣሥ 31/2017 ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ወንጀሎቹ የተፈጸሙት ቲታመድ በተሰኘው በሚያንማር የጦር ኃይል፣ በብሔራዊ የፖሊስ ኃይሎች፣ በድንበር ጥበቃ ፖሊሶች እንዲሁም የሮሂንጋ ማንነት በሌላቸው ሲቪሎች እገዛ ነው፡፡ በግዳጅ እንዲሰደዱ ከተደረጉት ባሻገር ወደ አስር ሺሕ ገደማ የሮሂንጋ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡

በሚያንማር ፕሬዝዳንት ላይ የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ የጠየቀው ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት፤ ባለፈው ሳምንት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ በፈጸመው ወንጀል መነሻ የእስር መዘዣ መቁረጡ የሚታወስ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2002 በተቋቋመው ፍርድ ቤት፤ በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular