Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችቢን ሰልማን፣ ኤርዶጋን እና አል ሲሲ በሪያድ ጉባዔ

ቢን ሰልማን፣ ኤርዶጋን እና አል ሲሲ በሪያድ ጉባዔ

የሙስሊም ሀገራት መሪዎች ሰኞ ኅዳር 2/2017 በሳዑዲ ዐረቢያ መዲና ሪያድ ያከናወኑትን ጋዛን እና ሊባኖስን የተመለከተው ጉባዔ አጠናቀዋል፡፡ የዐረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ሀገራት ድርጅት አባላትን በጋራ ያሰባሰበው ጉባዔ ሲጠናቀቅ የወጣው መግለጫ፤ እስራኤል በወረራ የያዘቸውን የፍልስጤም መሬት በመልቀቅ እንድትወጣ ጥሪ የቀረበበት ነው፡፡

በስብሰባው መዝጊያ የተነበበው ይህ መግለጫ የፍልስጤም መሬት ድንበሩ እ.አ.አ ከ1967 በፊት በነበረው እንዲጸና ተጠይቋል፡፡ በጉባዔው የተሳተፉት የ57 ሀገራት መሪዎች የፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገርነት እውን እንዲሆን በመጠየቅ ለትግበራውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን መጠነ ሠፊ ጥቃት ያወገዘው የሙስሊም ሀገራት መሪዎች ጉባዔ፤ “አስከፊ እና አስደንጋጭ” ሲል የጠራውን ጥቃት “ከዘር ፍጅት” ጋር የሚተካከል ነው ብሎታል፡፡

የጉባዔው አስተናጋጅ ሳዑዲ ዐረቢያ በልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ተወክላ ድምጽዋ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ንግግር ቢን ሰልማን የእስራኤልን ጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ “የዘር ፍጅት ነው” ሲሉ ጠርተውታል፡፡ በተጨማሪም ስለ መስጂደል አቅሷ ያነሱት አልጋ ወራሹ፤ “[እስራኤል] በመስጂደል አቅሷ ላይ ርኩሰት ፈጽማለች” በማለት የወራሪ ወታደሮችን ድርጊት ኮንነዋል፡፡ ከጋዛ ውጪ የእስራኤል ወታደሮች በሊባኖስ የሚፈጽሙት ጥቃትም በቢን ሰልማን ንግግር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ ድርጊቱን እንዲያስቆም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በጉባዔው ላይ ሌላኛው ተናገሪ የነበሩት የግብጹ ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አልሲሲ ናቸው፡፡ አል ሲሲ በንግግራቸው የጋዛን ጉዳይ ቢያነሱትም እንደ ቢን ሰልማን የእስራኤልን ጥቃት “የዘር ፍጅት ነው” ከማለት ተቆጥበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህን ከማድረግ ቢቆጠቡም “ታቅዶበት የሚፈጸም ነው” ያሉትን ድርጊት ከማውግዝ ግን ወደ ኋላ አላሉም፡፡ አክለውም “የፍልስጤምን ጉዳይ ለመቀልበስ የሚሞክሩትን፣ በግዳጅ የሚያፈናቅሉትንም ሆነ ጋዛን ለነዋሪነት ለማትመች የሚደረገውን ጥረት ሁሉ የምንቃወመው መሆኑን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በዐረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ሀገራት ድርጅት ጥምረት በተሰናዳው ጉባዔ ላይ የተናገሩት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋንም እንዲሁ በጋዛ የሚሰነዘረውን ጥቃት በማውግዝ፣ የእስራኤልን “ፍልስጤማዊያንን የማጥፋት እቅድ” ኮንነው ለእቅዱ የሚንቀሳቀሱትን አስጠንቅቀዋል፡፡ ኤርዶጋን በንግግራቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ለእስራኤል “ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና ሞራላዊ ድጋፍ” ይሰጣሉ ያሏቸውን ምዕራባዊያን ሀገራትን ነው፡፡ በሌላ በኩል በፍልስጤማዊያን ላይ ለሚፈጸመው የዘር ፍጅት የሙስሊሙ ዓለም በአንድነት መቆም አለመቻሉንም ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ መሆኑን በመናገር በትብብር እንዲቆሙ በመድረኩ ላይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሪያዱ የሙስሊም እና ዐረብ ሀገራት ጉባዔ የተከናወነው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ዶናልድ ትራምፕ መሆናቸው ይፋ ከተደረገ አንድ ሳምንት እንኳ ሳይሞላ መሆኑ በተለያዩ ተንታኞች ዘንድ የተለያየ አስተያየት እንዲሰጥበት አድርጓል፡፡ ለአል ዐረቢያ የተናገሩት የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ተንታኙ አና ጃኮብስ፤ ጉባዔው የቀጣናው ሀገራት ከትራምፕ አስተዳደር የሚፈልጉት ምን እንደሆነ “ፍንጭ የሰጡበት ጥሩ አጋጣሚ ነው” ብለዋል፡፡ የተንታኙን አስተያየት የሚጋራ የሚመስል አስተያየት በኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ሪዛ አሪፍ በጉባኤው ላይ ተስተጋብቷል፡፡ አሪፍ በመድረኩ ዓለም ትራምፕ በጋዛ እና በሊባኖስ በንጹሐን ሰዎች ላይ የተከፈተውን ጦርነት “በአስቸኳይ ያስቆማሉ በሚል እየጠበቀ ይገኛል” ብለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular