Homeዜናና ወቅታዊዜናበፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል የተባለ የጥናት ሠነድ ለምክር ቤቱ...

በፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል የተባለ የጥናት ሠነድ ለምክር ቤቱ ቀረበ

በፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል የተባለ የጥናት ሠነድ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መቅረቡ ታወቀ፡፡ ለምክር ቤቱ የቀረበው ሠነድ ካስቀመጣቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ ለውጥ እንዲደረግ፣ የሐብት አሰባሰብ እና አስተዳደር እንዲሁም የድጋፍ ሠራተኞችን ለውጥን የሚጠይቀው እንደሚገኝበት ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን መሠረት በማድረግ የቀረበውን የጥናት ሠነድ፤ ባለፈው ዓመት አጋማሽ የተቋቋመው አጥኚ ኮሚቴ ኅዳር 2/2017 ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ አስረክቧል፡፡ ሠነዱን ያስረከቡት የጥናት ኮሚቴው አባላት የሆኑት ዶክተር ሸይኽ ሙሐመድ ሐሚዲን እና የሕግ ባለሞያው ዓብዱልሐኪም ጀማል መሆናቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሠራር ሒደቱ የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል የተባለ የጥናት ሠነድ የተዘጋጀለት የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት፤ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ አዲስ የተዘጋጀው የጥናት ሠነድ የተዘጋጀውም በፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ኮሚቴ እንዲቋቋም ባስተላለፉት ትእዛዝ መሠረት መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” በጥናቱ ሒደት ላይ ከተሳተፉ የሕግ ባለሞያ ሰምቷል፡፡ እንደ ሕግ ባለሞያው ከሆነ ለጥናቱ መነሻ የሆነው በተደጋጋሚ “ከተገልጋዮች የሚቀርበው ቅሬታ” ነው፡፡ በቅሬታነት ይቀርባሉ ከተባሉት ጉዳዮች መካከል የፍርድ ቤቶቹ “የአገልግሎት አሰጣጥ” እና “ተቋማዊ አቋም ይገኝበታል፡፡

 
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የጥናቱን ሠነዱን በተረከቡበት ወቅት/EIAC

ይህንኑ ተከትሎ ቀድሞ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ውስጥ በሚገኘው የዑለማእ ኮሚቴ አማካኝነት የመጀመርያ ጥናት መከናወኑም ነው የታወቀው፡፡ ከዚህ በኋላ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በተቋቋመው ኮሚቴ ደግሞ አምስት አባላት ያሉት የፍርድ ቤቶቹን ችግር በዝርዝር የሚያቀርብ ኮሚቴ ተዋቅሯል ያሉት የሕግ ባለሞያው፤ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ተካተዋል ያሏቸው አባላት የተመረጡት “ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከሕግ ባለሞያዎች፣ ከሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ እና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም ከጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ” ናቸው፡፡

የሕግ ባለሞያው እንደሚሉት “ሠፊ ጥናት ተደርጎበታል” ያሉትን ያሉትን ሠነድ ለማዘጋጀት በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ የሚገኙ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ላይ ግምገማ ከማድረግ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሣሣይ ሥርዐት ካላቸው ሀገራት ተመክሮ ተወስዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠንካራ አዋጅ አላቸው የተባሉ የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ሠነዶች ለማየት ተሞክሯል፡፡ ለተዘጋጀው ሠነድ ተመክሮ ተወስዶባቸዋል ከተባሉ ሀገራት መካከል የሃይማኖት እና መንግሥት ልዩነት ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥ በኬንያ፣ ዛንዚባር እና ናይጄሪያ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አሠራር ታይቶ መካተት የሚችሉት የሠነዱ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከክልሎችም እንዲሁ የትግራይ፣ አፋር እና ሶማሌ አዋጅ በግብዐትነት ተወስዷል ተብሏል፡፡ የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ጥናት በሚደረግበት ወቅት ከፌዴራሉ የተሻለ ሆነው መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡

ኮሚቴው ጥናቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሦስት ጉዳዮች ላይ ለውጥ ሊደረግ ይገባል በሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን የሚገልጹት በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ባለሞያ፤ እነዚህ ጉዳዮች የሕግ ማዕቀፍን፣ የሐብት አስተዳደርን እና የሰው ሐብት አስተዳደርን የሚመለከቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፍን በተመለከተ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ “የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን የሚገድብ” በመሆኑ መሻሻል አለበት የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፉን በተመለከተ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን አቋም ለማጠናከር በ1992 የፀቀደው አዋጅ እንደሚያመለክተው ፍርድ ቤቶቹ “የወል የዳኝነት ሥልጣን የሚኖራቸው” ተብሎ የተቀመጠው ውስን ጉዳዮች ላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በአዋጁ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን የሚጋሩት ከመደበኛው ፍርድ ቤቶች ጋር ሲሆን፣ በዚህም ፍርድ ቤቶቹ “የወል ሥልጣን” እንጂ የራሳቸው ልዩ ሥልጣን የላቸውም እንደሌላቸው ይጠቅሳል፡፡ በአዋጁ በቀዳሚነት የተቀመጠው “የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናት ሞግዚትነት” ነው፡፡ ይህ አዋጅ በሁለተኛነት ያስቀመጠው “የወቅፍ፣ የሥጦታ ወይም የኑዛዝ ጉዳዮችን” የያዘ ነው፡፡

በአዲሱ ጥናት ከሰው ሐብት ጋር በተገናኘ በተለይ በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ይስተዋላል የተባለው እስላማዊ አለባበስ ካለመኖር አንስቶ ከእስልምና ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ስለሚስተዋሉ በአፋጣኝ ለውጥ እንዲደረግ ጥናት በምክረ ሐሳብ ማስቀመጡን የሕግ ባለሞያው አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል በሐብት አሰባሰብና አስተዳደር ፍርድ ቤቶቹ በአሁኑ ወቅት ካሉበት የተሻለ ቁመና እንዲኖራቸው የራሳቸውን ሕንጻ እንዲገነቡ የግንባታ ቦታ እንዲሰጥ እንዲሁም በጀተን የተመለከተውም መቅረቡ ታውቋል፡፡

በሠነዱ የተጠቀሰውን የሕንጻ ግንባታ መሬት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ፍርድ ቤቱ የሕንጻ ግንባታ ቦታ እንዲያገኝ የሚያስችል ንግግር መኖሩ ተነግሯል፡፡ በኢትዮጵያ በመንግሥት ድጋፍ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት በ1934 ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular