የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን፤ የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ለፈጸመው ሁሉ ተጠያቂ እንዲደረግ ሀገራቸው አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ይህን የተናገሩት በሳዑዲ ዐረቢያ እና አዘርባጃን ጉብኝታቸው ወቅት ለጋዜጠኞች በአውሮፕላን ውስጥ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡
በዚሁ ቆይታ ቱርክ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ውስጥ ለፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ አቅሟ የሚፈቅደውን ሁሉ እንደምታደርግ አጽኦት ሰጥተው በመግለጽ፤ አስተዳደራቸው ከእስራኤል ጋር “አቋርጦታል” ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የማስቀጠል ምንም ዐይነት ፍላጎት እንደሌለውም ጠቁመዋል፡፡
ኤርዶጋን “[የቱርክ መንግሥት ከዚህ ቀደም] ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቋረጥ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ፀንቷል፣ እኛም ለወደፊቱ ይህን አቋም አስጠብቀን እንጓዛለን” ብለዋል፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በእስራኤል ላይ የንግድ ማዕቀብ ቢጥልም አንካራ ግን አሁንም ድረስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን መቀጠሏን የሚል ኢስት ዐይ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ዘገባው ለዚህ አስረጂ ያደረገው የቱርክ መንግሥት ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት በእስራኤል ይገኘ የነበሩትን አምባሳደሩን ለመመካከር በሚል በይፋ ቢጠራም በቴል አቪቭ የሚገኙ የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች በሥራ ላይ መገኘታቸውን ነው፡፡ በአንጻሩ የእስራኤል ባለሥልጣናት በአንካራ ይገኝ የነበረውን ኤምባሲያቸውን ከሥራ ውጪ አድርገዋል፡፡ ለዚህ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው ቀጣናው “የፀጥታ ሥጋት” አለበት የሚል ነው፡፡
በሌላ በኩል ኤርዶጋን የሚመሯት ቱርክ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ፍልስጤምን በመደገፍ እና በእስራኤል ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል በመደገፍ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ መቀላቀሏን ይፋ አድርጋለች፡፡ ይህ ክስ በደቡብ አፍሪካ የቀረበ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ከሰሞኑ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ጥሪውን የተመለከተው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበ አቤቱታ ላይ 52 ሀገራት ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ፊርማ አሰባስባው ማስገባታቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የእስራኤል ወታደሮች ባለፉት 13 ወራት ብቻ በንጹሐን ፍልስጤማዊያን ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 43 ሺሕ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከተገደሉት መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ሕጻናት እና እናቶች ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












