የቱርክ የደኅንነት ባለሥልጣናት የፍልስጤሙ ሐማስ ጽሕፈት ቤቱን ወደ ሀገራቸው ያዞር ነው መባሉን አስተባበሉ፡፡ ቡድኑ ከኳታር የመልቀቅ እድል ቢኖረው እንደ ኢራን፣ አልጄሪያ እና ኢራቅ ያሉ ሀገራት አማራጭ መዳረሻ ሊሆኑት ይችላል በሚል እየተነገረ ይገኛል፡፡
የቱርክ የደኅንነት ባለሥልጣናት የሐማስ ጽሕፈት ቤቱን ወደ ሀገራቸው ሊያዞር ነው መባሉን ያስተባበሉት ቡድኑ መቀመጫውን ካደረገበት “ኳታር ሊወጣ ነው” የሚሉ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸው የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ከወጡ በኋላ ነው፡፡
ከቀናት በፊት ቢቢሲ እና ሲኤኤንን ጨምሮ ምዕራባዊያን የዜና ወኪሎች መነሻውን እስራኤል ያደረገ “ሐማስ በዶሐ የሚገኘውን የፖለቲካ ጽሕፈት ቤቱን እንዲዘጋ ኳታር ከአሜሪካ ጋር ተስማምታለች” የሚል ዘገባ ይዘው ወጥተዋል። ነገር ግን ዘገባውን ይዘው ከወጡት መካከል የሆነው ሲኤንኤን ሥማቸው ያልተጠቀሰ የሐማስ ከፍተኛ ኃላፊ ለመረጃው ማስተባበያ ሰጥተውኛል ብሏል፡፡ በአትላንታ ጆርጂያ መቀመጫውን ያደረገው የመገናኛ ብዙኃን ዋቢ ያደረጋቸው እኒህ ባለሥልጣን፤ መረጃውን ሐሰተኛ መሆኑን በመግለጽም አጣጥለውታል፡፡ ባለሥልጣኑ “በአሜሪካ ጥያቄ መሠረት ኳታር ሐማስን ከዶሐ ለማስወጣት መስማማቷን በተመለከተ በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የተዘገበው መረጃ መሠረት ቢስ እና ጫና ለማሳደር የተደረገ ሥልታዊ አካሔድ ነው” ብለዋል፡፡ መረጃው ማስተባበያ ቢሰጥበትም ቡድኑ ኳታርን ከለቀቀ ቀጣይ መዳረሻው ቱርክ ልትሆን ትችላለች የሚል መላምት በዚሁ ዘገባ ላይ ሠፍሯል፡፡
ሆኖም “ቱርኪዬ ቱዴይ” የተሰኘ የዜና ወኪል ዛሬ ሐሙስ ባስነበበው ዘገባ የቱርክ የደኅንነት ኃላፊዎች ሐማስ በሀገሪቱ ቋሚ ቢሮ ለመክፈት ምንም ዕቅድ እንደሌለው በመግለጽ መላምቱን ውድቅ ማድረጋቸውንም አስነብቧል። በዘገባው የተጠቀሰ በኳታር የሐማስ እንቅስቃሴዎችን ያውቃል የተባለ አንድ ምንጭ እንደገለጸው፤ ኳታር ሐማስ “በዶሐ ውስጥ ያለውን ቢሮ እንዲዘጋ ጥያቄ አላቀረበችም”።
የሐማስን ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች ቡድኑ ምናልባት ከኳታር የሚለቅ ከሆነ መዳረሻ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚገምቷቸውን ሀገራት መዘርዘር ጀምረዋል፡፡ በዝርዝሩ ከተካተቱት ውስጥ ኢራን፣ አልጄሪያ እና ኢራቅ ይገኙበታል፡፡ የቀድሞው የኔቶ ቋሚ መልእክተኛ መሐመድ ፋቲሕ ሴይላን በበኩላቸው ለመገናኛ ብዙኃን እንዳሉት፤ ሐማስ በቅርቡ የተፈፀሙበትን የመሪዎቹን ግድያ ተከትሎ የአመራር መንገዱ ከዚህ ቀደም በነበረበት ላይቀጥል ይችላል፡፡ ሙሐመድ ፋቲህ ሐማስ በአንድ ማዕከላዊ ቦታ መቀመጫውን ከማድረግ ይልቅ በተለያዩ የዐረብ ሀገራት ቢሮዎችን ሊከፍት የሚችልበት ዕድል እንዳለው ግምት ሰንዝረዋል፡፡
ሐማስ ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስማኢል ሐኒያህ በኢራን ቴህራን ከተማ፤ እንዲሁም ተተኪስ ያህያ ሲንዋር ደግሞ በጋዛ ሰማዕት ሆነዋል ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ቡድኑ የያሕያ ሲንዋርን ተተኪ እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረገም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












