የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሔድ የቆየውን ስድስተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሲያጠናቅቅ፤ ሸይኽ ጋሊ ሙኽታርን ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡን አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ አዲስ ፕሬዝዳንት የመረጠው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀማል ሙሳ “በገዛ ፍቃዳቸው የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ” በማቅረባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ ጥቅምት 30/2017 እና ኅዳር 1/2017 ባካሔደው ጉባኤ ፕሬዝዳንቱን በሸይኽ ጋሊ ሙኽታር በአዲስ መተካቱን ሲገልጽ፣ ሸይኽ ጣሂር ዓብዱልቃድርን በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ሸይኽ ዚያድ ዓሊን ምክትል ፕሬዝደንት አድርጎ መምረጡንም የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡስታዝ ሹዓይብ ሸምሱ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ቅዳሜ እና የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የ2016 በጀት አፈጻጸም ሪፖርት የተደመጠበት እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት እቅድ የጸደቀበት እንደነበርም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተከናወነው የሰባተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ከነበረበት ጊዜ “ዘግየት ብሎ መደረጉን” ያነሱት ኡስታዝ ሹዐይብ፤ ለዚህ ምክንያት ሆኗል ያሉት “የግምገማ ውጤቶች እስኪስተካከሉ ድረስ” ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡

ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች እና ከተሞች ከእያንዳንዱ ሦስት ሰው ተሳታፊ ሆኖበታል በተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአጠቃላይ ከ43 ዞኖች እና ከተሞች 127 ተወካዮች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሥራ አፈጻጸም እና ቀጣይ እቅዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው የጸደቀ ሲሆን፣ የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ የተከናወበት ሆኖ ማለፉንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
የአመራሮችን ምርጫ የተደረገው ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ጀማል ሙሳና ምክትሎቻቸው “በፍቃደኝነት” እንዲሁም “በሕመም ምክንያት” የሥራ መልቀቂያ በማቅረባቸው ነው ተብሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በጉባኤው ፊት ቀርበው “ከእኔ የተሻለ ሰው መምጣት አለበት” ማለታቸውን የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ማሕሙድ ሑሴን ከለቀቁ ወደ አምስት ወር ገደማ በመሆኑ በምክር ቤት ይኸው በይፋ መቅረቡ አክለዋል፡፡ ሸይኽ ሙሳ ዐብዱረሕማንም እንዲሁ በሕመም ምክንያት ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ በማቅረባቸው ሦስቱንም ኃላፊዎች መተካት ግዴታ ሆኗል ተብሏል፡፡
መልቀቂያው የቀረበለት ጉባኤው በሥራ አስፈጻሚው በኩል ሦት ዕጩዎችን በማቅረብ አባላት ድምጽ እንዲሰጡበት ማድረጉ ሲገለጽ፣ በዚህም ከፍተኛ ድምጽ አግኝተዋል የተባሉት ሸይኽ ጋሊ ሙኽታር ሸይኽ ጀማል ሙሳን እንዲተኩ ተመርጠዋል ተብሏል፡፡ ሸይኽ ጋሊ ከአባላት አግኝተውታል የተባለው ድምጽ ሃምሣ ነው፡፡
አዳዲስ አመራሮችን መምረጡን ያሳወቀው የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ በቀጣይ በጀት ዓመት ቅድሚያ የሚሠጣቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የ100 ቀናት እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን አሳውቋል፡፡
የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ የተከናወነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ካካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የእስልምና ጉዳዮ ከፍተኛ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












