Homeዜናና ወቅታዊዜናየሙስሊሙ ዓለም መሪዎች በጋዛ እና ሊባኖስ ጉዳይ በሪያድ ከተማ መምከር ጀመሩ

የሙስሊሙ ዓለም መሪዎች በጋዛ እና ሊባኖስ ጉዳይ በሪያድ ከተማ መምከር ጀመሩ

የእስላማዊ ትብብር ሀገራት ድርጅት እና የዐረብ ሊግን ያጣመረው ልዩ የምክክር ጉባዔ ትኩረቱን በጋዛ እና በሊባኖስ ላይ በማድረግ መካሔድ ጀምሯል፡፡ እሑድ ኅዳር 1/2017 በሳዑዲ ዐረቢያ ሪያድ መካሔድ በጀመረው ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸው ታውቋል፡፡

በመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ የጉባዔው አስተናጋጅ ሳዑዲ ዐረቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚህ ንግግር ወቅት አልጋ ወራሹ እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡ በሳዑዲ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባዔ አምና በተመሳሳይ ወቅት የተከናወነ ሲሆን፣ የአሁኑ የዚያን ጊዜው ተከታይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሳዑዲ የዜና አገልግሎት ስለ ጉባዔው ይዞት በወጣው ዘገባ ጉባዔተኞቹን ያሰባሰበው “እየተባባሰ የመጣው” በፍልስጤም እና በሊባኖስ እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት ነው፡፡ የዜና ኤጀንሲው ከጉባዔው የተለያዩ ውጤቶች እንደሚጠበቅም ዘርዝሯል፡፡

ከተዘረዘሩት መካከል ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያላቸው “የንጹሐንን ጥቃት ማስቆም፣ ለፍልስጤማዊያንና ለሊባኖስ ሕዝቦች ድጋፍ ማድረግ፣ በጉዳዩ ላይ ወጥ አቋም መያዝ፣ ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ርምጃዎችን እንዲወስድ ጫና ማሳደር” ተካተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን በዛሬው እለት ሪያድ መግባታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ኤርዶጋን ሪያድ ሲደርሱ የመዲናዋ አሚር ፈይሰል ቢን ባንዳር ቢን ሡልጣን አቀባበል አድርገውላቸዋል ተብሏል፡፡ በጉባዔው ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሬዝዳንቱ፣ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽውን ጥቃት ለማስቆም “በሙስሊም ሀገራት መካከል ትብብር እንዲደረግ” ጥሪ ያስተላልፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባዎቹ አመልክተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተከናወነው ተመሳሳይ ጉባኤ ቱርኪዬን ጨምሮ ሳዑዲ ዐረቢያ እና ግብጽን ያካተተ “የጋዛ ኮንታክት ግሩፕ” የተሰኘ ጥምረት ተመሥርቶ ነበር፡፡ ኳታር፣ ፍልስጤም፣ ኢንዶኔዥያ እና ናይጄሪያ የተካተቱበት ይህ ስብስብ በጋዛ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲመከር መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ፍልስጤም እና እስራኤል ሁለት ሀገር እንዲሆኑ ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡

እስራኤል ባለፉት አስራ አራት ወራት በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 3 ሺሕ 500 ንጹሐን ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular