Homeዜናና ወቅታዊዜናኤርዶጋን፤ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እስራኤል በጋዛ የምትሰነዝረውን ጥቃት ለማስቆም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ...

ኤርዶጋን፤ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እስራኤል በጋዛ የምትሰነዝረውን ጥቃት ለማስቆም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጠየቁ

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ የምትሰነዝረውን ጥቃት ለማስቆም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጠየቁ። ኤርዶጋን ትራምፕ አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያስቆማሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ይህን የጠየቁት ወደ ሀንጋሪ የሚያደርጉትን ጉዞ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው። ከጋዛ በተጨማሪም እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትሰዝረውን ጥቃትም ተመራጩ ፕሬዝዳንት እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ ትራምፕ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሲከተሉ የቆዩትን ፖሊሲ ትራምፕ ማስቀጠል እንደሌለባቸው ተናግረዋል። የፕሬዝዳንት ባይደን ፖሊሲ የቀጣናውን ችግሮች አባብሶታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

በአሜሪካ ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲን የወከሉት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ፉክክሩን ማሸነፋቸው ይፋ የተደረገው በሳምንቱ አጋማሽ ነበር። ውጤቱን ተከትሎ ኤርዶጋን ለትራምፕ በመደወል የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ለጋዜጠኞች ነግረዋቸዋል።

የትራምፕ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ እንደ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ሁሉ በአሜሪካን ሀገር የሚገኘው የመብቶች ተሟጋቹ ዘ ካውንስል ኦፍ አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ፤ ተመራጩ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሙስሊሞችን በተመለከተ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጠይቋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ኒሐድ አዋድ ባወጡት መግለጫ፤ በምርጫው የትኛውም ግለሰብ ቢያሸንፍ ችግር እንደማይሆን በመጠቆም፣ “መሠራት ያለበት ጉዳይ መኖሩን” አጽንኦት ሰጥተው ጽፈዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ “በምርጫው ወደ ሥልጣን የወጡ ባለሥልጣናት ሙስሊም መራጮች ያነሷቸውን ጉዳዮች በቅንነት እንዲያጤኑት እንጠይቃለን፣ ይህ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕም ይሠራል” ብለዋል።

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሐላ ፈጽመው የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ከጆ ባይደን ይረከባሉ ተብሎ የሚጠበቀው ጥር 12/2017 ነው፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular