Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየጥንቱን ፍለጋ፡- ከአንደሉስ እስከ መካ

የጥንቱን ፍለጋ፡- ከአንደሉስ እስከ መካ

ከሠላሳ አራት ዓመታት በፊት ነው – እ.አ.አ በ1990፡፡ ስፔናዊው ራፋኤል ፈርናንዴዝ ከእስልምና ጋር ተዋወቀ፡፡ መምሕሩና የጂኦግራፊ አጥኚው ሰው አላህ ልቡን ወደ እውነት ስለመራው ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ ደስታው በትኩሱ ሳለ ለጌታው የገባው ቃል እንዲህ የሚል ነበር – “ሐጅ የማደርገው በፈረስ ተጉዤ ነው”፡፡ ይህ ለወቅቱ ጉልበታም ወጣት በአንድ ጊዜ የሚቻል አልነበረም፡፡ ጉልበት ብቻ አይደለም፣ ጊዜ እና ገንዘብ የሚጠይቅ ቃል ኪዳን ነበር፡፡ ጉልበት፣ ጊዜ እና ገንዘብ ቢሟላም ጽናት የሚጠይቅም ነበር፡፡ ስለዚህ መታገስ ነበረበት፡፡

ዐብደላህ ፌርናንዴዝ በወጣትነት ዕድሜው

ከ35 ዓመታት በኋላ የዚያን ጊዜው ወጣት ራፋኤል ፈርናንዴዝ፤ በእስልምና ሥሙ ዓብደላህ ተብሎ የሚጠራ ሆኗል፡፡ ዓብደላህ በዩኒቨርሲቲ ባጠናው ጂኦግራፊ፣ በዲግሪ ላይ ሌላ ዲግሪ እየደረበ የዶክትሬት ማዕረግ ላይ ደርሷል፡፡ በትምሕርት ረዥም ርቀት በመጓዝ ብቻ ሳይወሰን ወጣት ሳለ ቃል ኪዳን ገብቶ ያልፈጸመውን ሐጅን በፈረስ ጀርባ ተንጠላጥሎ ወደ ቅዱሳኑ ሥፍራዎች የመድረስ ውጥን ለማማላት ዝግጁ ሆኗል፡፡

ዓብደላህ በዚህ መልኩ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ሲነሳ አርዓያ ያደረገው ከ500 ዓመታት በፊት በአንደሉስ ምድር የነበሩ በጀግንነት የሚያወድሳቸውን አያት ቅድመ አያቶቹን ነው፡፡ በጉዞው አያት ቅድመ አያቶቹንም አብሮ ያስታውሳል፡፡ በርግጥ የፈረስ ግልቢያ መውደዱ፣ ከዚያም ሲያልፍ በአንዳንድ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ማሸነፉ ይህን መንገድ እንዲመርጥ አስችሎታል፡፡ ዓብዱላህ የቅድመ አያቶች አንደሉስ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ሥፍራዋ ከፍ ያለ መሆኑንም ያውቃል፡፡ እነርሱ ያን ጊዜ የጌታን ትእዛዝ ለመሙላት ፀሐይ እና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ሀገራትን አቋርጠው ከ8 ሺሕ ኪሎ ሜትር በኋላ ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሚደርሱም ከድርሳናት አንብቧል፡፡

ዓብዱላህ ፌርናንዴዝ ያለፉት ዓመታት ይህን ገድል ለመድገም የተጋበት ነበር፡፡ የጉዞ እቅድ ነደፈ፣ ራሱን የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በማድረግ ይህን ፅናት የሚጠይቅ ጉዞ በማድረግ በርትተው የሚያበረቱን ባልንጀሮች መፈለግ ጀመረና የሕልሙን ተጋሪዎች አገኘ፡፡ እነዚህ የሕልም ተጋሪዎቹ ሙሐመድ ሚስባሂ፣ እስማኢል ጎንዛሌዝ፣ ዑመር ከሪም፣ ሙጃሂድ ኤስፒኖ፣ ዑመር ሚላኒሮ እና ዓብዱልቃድር ሃርካሲ ሆኑ፡፡ ዓብዱላህ ሕልሙን የሚጋሩትን ሰዎች ከማግኘት ውጪ ሌሎች መሟላት የሚኖርባቸው ሎጂስቲክሶችን ለማግኘት እንቅስቃሴውን ቀጠለ፡፡ ሰዎቹን 8 ሺሕ ኪሎ ሜትር አቆራርጠው ሳዑዲ ዐረቢያ ምድር ላይ የሚያደርሱ ብርቱ ፈረሶችን መፈለግ ተጀመረ፡፡ የትኞቹ ዝርያዎች የተሻለ ብርታት፣ ቅልጥፍና እና ጉልበት አላቸው ብሎ መምረጥ ስለነበረበትም በማፈላለግ የዐረቢያ ዝርያ ያላቸው ፈረሶችን ለጉዞው ተስማሚ ሆኖ አገኛቸው፡፡ ፈረሶቹን ማሠልጠንና ምግባቸውን እየመረጡ ጡንቻቸው እንዲፈረጥም ማድረግ የእለት ተእለት ሥራው ሆነ፡፡ ብርታት የሚጨምሩ ተግባራት ሲደረጉ የነበሩት ለፈረሶቹ ብቻ ግን አልነበረም፡፡ የጉዞው ተሳታፊዎችም ይህንኑ ሲከውኑ ቆዩ፡፡ በዚህ ሒደት የሕክምና ባለሞያዎች የሚያስፈልገውን እገዛ እያደረጉ ቆይተዋል፡፡

ቀጣዩ ሒደት የነበረው የፈረሶቹን ጉልበት መለካት ነበር፡፡ እነ ዓብዱላህም ወደፊት የሚጠብቃቸውን ብርታት የሚጠይቅ ጉዞ የሚሞክሩበት ቀን ተቆረጠ፡፡ ለሙከራው የተመረጠው የሰሜናዊ ስፔን ክፍል ነበር፡፡ 2021 ክረምት የመጀመሪያው የፈረስ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ዓብዱላህ እና የሕልም ተጋሪዎቹ ለአስራ ስድስት ቀናት ባደረጉት የፈረስ ላይ ጉዞ 700 ከሎ ሜትር መሸፈን ቻሉ፡፡ የፈረሱም የሰውም ጉልበት ተፈተሸ፡፡ ስለ ጉዞው እነ ዓብዱላህ ሲናገሩ “ፈታኝ ቢሆንም ስኬታማ ነበር” ይላሉ፡፡ ጉልበት ከሚፈትሸውና ከሌላው ሁሉ “ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖረን አድርጎናል” ብለዋል፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ ሌላ አንድ ዓመት ጠብቀው ሁለተኛው ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው፤ አደረጉት፡፡ በአጎራባች ፖርቹጋል በኩል ከሰሜን ወደ ደቡብ የተደረገው የፈረስ ላይ ጉዞ በ2022 የተደረገ ነበር፡፡ ይህ ጉዞ እንደቀደመው ጊዜ 16 ቀናት ሲፈጅ፤ የሸፈኑት 600 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ይህ ቁጥር ቀድሞ ከተመዘገበው ያነሰ ነው፡፡ እነ ዓብዱላህ ለዚህ ሰበብ የሆነው የአየር ሁኔታው በጣም ደረቅ መሆኑ እንዲሁም “በማናውቀው ሀገር እና ቋንቋ ጉዞውን ማድረጋችን ነው” ሲል ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ቢሆንም ለቀጣይ ጉዞ በርካታ ስንቅ የተያዘበት ነበር ይላል፡፡

ዓብደላህ ፌርናንዴዝ (ፒኤችዲ)

አሁንም ይህ ብርታት የሚጠይቅ ልምምድ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከወራት በፊት ከአንደሉስያ ምእራባዊ አካባቢ የተነሱት እነ ዓብዱላህ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ከረር ባለ ፀሐይ ውስጥ ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቀኑ ከረር ያለ ፀሐይ ቢያስተናግድም ሌሊቱ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ የሚባል ስለነበር ከሁለቱ የልምምድ ጉዞዎች ለየት ያለ አጋጣሚ ማስተናገድ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህ የአየር ጠባይ 420 ኪሎ ሜትር ሸፍነው ተመለሱ፡፡ በተለይ በምሽት በደረሱበት እሳት እያቀጣጠሉ መሞቅ ግድ ነበር፡፡ በፈረስ ላይ ከአንደሉስ ምእራብ አቅጣጫ ወደ ምሥራቅ ተጉዘው ግራናዳ ሲደርሱ የተወሰኑ ሰዎች አቀባበል አደረጉላቸው፡፡

አሁን ልምምዱ አበቃ፡፡ የፈረስ ላይ የሐጅ ተጓዦቹ ቀድመው እቅድ ሲያወጡ አላህ ቢፈቅድ መድረስ የሚፈልጉት በዚህ ዓመት በሚከናወነው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ነው፡፡ ሆኖም ከፊታቸው ስምንት ሺሕ ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከደቡባዊ ስፔን ተነስተው፣ ዐስር ሀገራትን ያቆራርጣሉ፡፡ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ስሎቬንያ፣ ክሮሽያ፣ ቦስንያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ኮሶቮ፣ ሰሜን ሜቄዶንያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቱርክ ደርሰው ቀይ ባህርን በጀልባ ተሳፍረው ግብጽ መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከግብጽ ደግሞ ቅዱሳኑን ሥፍራዎች ወደያዘችው ሳዑዲ ዐረቢያ መጓዝም አለ፡፡

ይህ 35 ዓመት ያስቆጠረን ቃል ኪዳን ለመሙላት የሚደረገው ጉዞ ከ23 ቀናት በፊት ተጀመረ፡፡ ዶክተር ዐብዱላህ ፌርናንዴዝ ዝግጅቱን ሲጀምሩ ከስድስት ሰዎች ጋር የነበረ ቢሆንም እንደ አለመታደል አሁን የጉዞው ተሳታፊዎች አራት ቀርተዋል፡፡ የእንስሳት ሐኪም፣ ነርስ፣ ምግብ አብሳይ እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያስፈጽሙ ሰዎችም በመኪና ይከተሏቸዋል፡፡ ሕልም የሚመስለው ለአላህ የተገባን ቃል ኪዳን የመሙላት ጉዞ እነ ዓብዱላህ ጥንት አያት ቅድመ አያታቻቸው እንዳደረጉት መነሻውን በአንደሉስ ውስጥ በሚገኘው አልሞናስቴር መስጂድ አድርጓል፡፡ ተጓዦቹ የእለቱ የት እንደደረሱ ኢንስታግራም እና ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ያጋራሉ፡፡ እስከ ትላንት ሐሙሰ ድረስም 935 ኪሎ ሜትር መጓዝ የቻሉት እነ ዓብዱላህ፤ ቀሪ ከ7 ሺሕ በላይ ኪሎ ሜትሮችን ለቃል በመታመን እና ቅዱሳኑን ሥፍራዎች በመናፈቅ ቀጥለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular