በመላው ዓለም ነጻነት እና ፍትሕ ናፋቂ ድምጾች ስለ ፍልስጤም ነጻነት መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ እንዲህ ዐይነቱ ክስተት አዲስ ባይሆንም የዚህ ሳምንት ተረኞች የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሆነዋል፡፡ ትናንት ረቡዕ ምሽት የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በበላይነት የሚያስተዳድረው የአሕጉሩ የክለቦች የእግር ኳስ ውድድር በተካሔደበት የፓሪስ ሴንት ዤርሜይን ስታዲየም ፓርክ ደ ፕሪንስ፣ ደጋፊዎች ስለ ፍልስጤም ነጻነት መፈክር አስተጋብተዋል፡፡ ደጋፊዎቹ ድምጻቸውን ያሰሙት 50 ሜትር የጎን ሥፋት እና 20 ሜትር ወደ ላይ በሚረዝም ጨርቅ ላይ መልዕክት በማሥፈር ነው፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የባለሜዳው የፓሪስ ሴንት ዤርሜይን ደጋፊ እንደሆኑ የተለዩ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ከፍ አድርገው ለካሜራዎች ባሳዩት መፈክር የፍልስጤምን ነጻነት ከመጠየቃቸው በተጨማሪ “በጋዛ ውስጥ የሚገኝ ሕፃን ነፍስ ዋጋው ከሌላው ያነሰ ነው ወይ?” የሚል ሞጋች ጥያቄ ያዘለ መልዕክት በስታድየሙ እንዲዘዋወር ማድረግ ችለዋል፡፡
ደጋፊዎቹ ያሰቡትን አሳክተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፤ የፈረንሳይ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ብሩኖ ግታሊዉ፤ የፓሪሱ ክለብ ደጋፊዎች የፍለስጤምን ነጻነት ማስተጋባታቸውን “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሰውዬው ይህን ቢሉም ሰሚ ያገኙ አይመስልም፡፡ አወዳዳሪው አካል የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ድርጊቱን ክለቡ ላይ የሚያስከትለው ቅጣት እንደማይኖር አሳውቋል፡፡ ማኅበሩ ስለ ጉዳዩ ለሬውተርስ የዜና ወኪል በሰጠው ማብራሪያ “የተጣሰ ደንብ የለም” ብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












