Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየሚንበር ቲቪ የአራተኛ ዓመት ማስታወሻ

የሚንበር ቲቪ የአራተኛ ዓመት ማስታወሻ

“ሁለንተናዊ ከፍታ” ላይ የመድረስ ራዕይ በመሰነቅ የሚንቀሳቀሰው ሚንበር ቲቪ ጁመዓ ጥቅምት 8/2017 ከተመሠረተ አራተኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ጣቢያው በዋነኛነት በሳተላይት እንዲሁም ዘመን በደረሰበት የዲጂታል አማራጭ ሁሉ ወደ ውድ ተመልካቾቹ ሲደርስ ቆይቷል፡፡ በዚህም እንደ ጣቢያ ይዞት ከተነሳው ራዕይና ሊደርስበት ከሚናፍቀው ከፍታ ለመድረስ ሲተጋ ነበር።

ጣቢያችን በአራት ዓመታት ቆይታው መነሻውም ሆነ መዳረሻ ያደረገው እስልምናን እና ሙስሊሞችን ነው፡፡ በመንገዳችን የሕዝበ ሙስሊሙ አንድነት ተጠብቆ እንዲጓዝ እና የእስልምና ሚዛናዊ አረዳድ እንዲሠርጽ ሙከራ አድርገናል። በቆይታችን በሚሊዮኖች ቤት መድረስ እንደቻልን በኢ-መደበኛ መንገድ ያደረግናቸው ዳሰሳዎች ይነግሩናል፡፡ በዲጂታል አማራጮች ሌሎች በርካታ ሚሊዮኖች ጋር ተገኝተናል፡፡ ከሀገር ቤት ተነስተን አትዮጵያዊያን ባሉበት የዓለም ከፍል መድረሳችንን ከተለያዩ ሀገሮች የሚላኩልን መልእክቶች አስረጂ ናቸው፡፡ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና ሌሎችም አካባቢዎች ሚንበር ቲቪ በሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ቤት መኖሩም ያኮራናል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ40 በላይ ፕሮግራሞችን ለተመልካቾች አድርሰናል፡፡ ከፕሮግራሞቹ ውስጥ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከአሁንም ድረስ የዘለቁ፣ ለአንድ ወይም ሁለት ዓመት አየር ላይ የሔዱ፣ ለወራት ያየናቸው፣ ሁነቶችን ብቻ መነሻ በማድረግ ለአንድ ጊዜ ብቻ የተላለፉ፣ በዕቅድ ብንይዛቸውም ከእነ አካቴው ወደ እናንተ ያላደረስናቸው አሉ፡፡

አብረውን የዘለቁ ፕሮግራሞች በእናንተ በተመልካቾች መልካም ፍቃድ ጭምር የቆዩ ናቸው፡፡ ተሳስተን ስንገኝ በማረም፣ ስንደክም በማበርታት፣ የጎደለ ሲኖር እያከማችሁ ስላቆያችሁን ምሥጋናው የእናንተ በመላው ዓለም የምትገኙ ተመልካቾች ነው – እናመሠግናለን፡፡ ለአንድ አልያም ሁለት ዓመት የዘለቁት፤ ጊዜ እና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ምናልባት ታርመው ደግመን የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡ በዕቅድ ይዘን ከእነ አካቴው ወደ ተመልካቾች ያላደረስናቸው ደግሞ ጊዜያቸው ሲደርስ ወደ እናንተ እንደሚቀርቡ ቃል እንገባለን፡፡ ለዚህ ጊዜ እና የምናዳብረው አቅም ምላሹን የሚሠጥ ይሆናል፡፡

በሒደቱ የመገናኛ ብዙኃን ሥራ በዋነኝነት የማኅበረሰብ ግልጋሎት እንደሆነ ስለምንረዳ እኛ የወሰድነው ሚና የአሳላፊ ነው፡፡ ይህን የምንለው በፍጹም ትሕትና ነው፡፡ በቆይታችን የፕሮግራሞቻችን መልክ ዐይነተ ብዙ ነበር፡፡ ሚንበር ቲቪ የእስልምናን እሴቶች ባከበሩ የመዝናኛ አማራጮች ቢገለጥ፣ ታሪክ ቢዘክር፣ ስለ ሰው ልጆች መብቶች ቢያነሳና መረጃ/ዜና ቢያቀርብ ሁሉም ጉዳይ ቀድሞ እንዳስቀመጥነው መዳረሻው እስልምና እና ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ከላይ እንደገለጽነው ሕልማችን የሕዝበ ሙስሊሙ አንድነት ተጠብቆ እንዲጓዝ አጋዥ መሆን እና የእስልምና ሚዛናዊ አረዳድ እንዲሠርጽ ማድረግ ነው። ይህን የምናደርገው/ያደረግነው በኃላፊነት እና በመልካም ኒያ ነው፡፡ የትኛውም ፕሮግራም ለሙስሊሞች ጠቀሜታ አለው በሚል ዓላማ ካልሆነ በጣቢያችን አልቀረበም፡፡ የተከተልነው መንገድ ወደፊትም የምንታመንለት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህን የምናስጠብቀው አንድም ዝግጅቶችን የምናቀርብለትን ማኅበረሰብ ከማክበር፣ ከዚያም ላቅ ባለ ሁኔታ የቆምንበት እስልምና ስለሚያስገድደን ነው፡፡

ሚንበር ቲቪ ከምሥረታው አንስቶ ያለ ፈተና እዚህ እንዳልደረሰ ሁላችንም የምንረዳው ነው፡፡ ክቡራን ተመልካቾች እንደሚያስታውሱት ጣቢያው በጥቅምት 2013 ሥራ ሲጀምር መላውን ዓለም ጭንቀት ውስጥ የዘፈቀው የኮቪድ19 ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ በተፈተነበት በዚህ ወቅት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን የሚጠይቀውን በራስ አቅም የቴሌቪዥን ጣቢያ የማቋቋም ውሳኔን በሥጋት ውስጥ ብናሳልፈውም፣ የፈራነው ቀርቶ ኃያሉ አላህ (ሱ.ወ) ብርታት ሰጥቶን አራተኛ ዓመት ላይ ለመድረስ አስችሎናል፡፡

የጣቢያችንን አራተኛ ዓመት ክብረ በዓል የምንዘክረው የሚንበር ቲቪ መሥራቾችን ጨምሮ ሁሉም ሠራተኞች የተቀበልነው ኃላፊነት ደረጃው ከፍ ያለ መሆኑን ለራሳችን በማስታወስ ነው፡፡ ይህ በአላህ (ሱ.ወ) ፍቃድ ከፊታችን ለምንጠብቃቸው የማኅበረሰባችንን ስብራት እንደ አቅማችን እንጠግንበታለን ብለን በውጥን ለያዝናቸው ዓመታት ቃል የምንገባበትም ጭምር ነው፡፡

በአራት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ለነበሩት የሚንበር ቲቪ መሥራች ባለድርሻዎች እንዲሁም እስካሁን ድረስ በአንድነት የዘለቁ ታላላቅ የንግድ ድርጅቶችን በተመልካቾቻችን ሥም ለማመሥገን እንወዳለን። ምሥጋናው ለጉዟችን ስንቅ አቀባይ ስለነበራችሁ እና የቀጣይ ሕልማችን ተጋሪ እንደምትሆኑ ስለምናውቅም ነው። በተለያዩ መንገድ ብርታት ለሆኑን የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና ለተመሣሣይ ዓላማ የተሰለፉ የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞችንም እናመሠግናለን። ሚንበር ቲቪ መቀመጫው አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም እንደ ራሳቸው ቤት በመቁጠር ከመላው ዓለም ሀገሮች አብረውን ለዘለቁ የዲያስፖራ ቤተሰቦቻችንም ምሥጋናችን ይድረስ፡፡

ሚንበር ቲቪ – አራተኛ ዓመቱን ሲያከብር ሁልጊዜም እንደሚለው ነገ ላይ ለመድረስ በትጋት እየሠራ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል።

ሚንበር ቲቪ – ሁለንተናዊ ከፍታ

4ኛ ዓመት ዛሬም እንደ ትላንት – በትጋት!

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular